ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ፡ በዘረ መል ምህንድስና የተሻሳሉ 750 ሚሊዮን ትንኞችን ልትለቅ ነው
በአሜሪካ፣ ፍሎሪዳ ግዛት በዘረ መል ምህንድስና የተሻሻሉ 750 ሚሊዮን ትንኞች እንዲለቀቁ ባለስልጣናቱ ፍቃድ ሰጥተዋል።
የተሻሻሉት ትንኞች በአየር ላይ የሚለቀቁት በሽታን የሚያስተላልፉ ተፈጥሯዊ ትንኞች ቁጥርንም ለመቀነስ ነው ተብሏል።
ከነዚህም መካከል የደንጊ፣ የወባና፣ ዚካ ቫይረስ የሚያስተላልፉ ትንኞች ይገኙበታል።
ፕሮጀክቱ የተጠነሰሰው ከአመታት በፊት ቢሆን በርካታ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ያልተጠበቀ አደጋ ሊያስከትል ይችላል በሚልም ሽንጣቸውን ገትረው በመከራከራቸው ከመተግበር ዘግይቶ ነበር።
አንደኛው ቡድንም በህዝቡ ላይ ጁራሲክ ፓርክን መፍጠር ነው ብሎታል። (በስቲቨን ስፒልበርግ የተሰራው ጁራሲክ ፓርክ ፊልም ዳይኖሰሮች ብቻ የሚኖሩበት ደሴትን ሊጎበኙ የሄዱ ሳይንቲስቶችን ታሪክ ያስቃኛል)።
ፕሮጀክቱ ፈቃድ ቢያገኝም የከባቢ ጥበቃ መብት ተሟጋቾች አሁንም ቢሆን ተፈጥሮን ሊያዛባ ይችላል እያሉም እያስጠነቀቁ ነው።
ለምሳሌም ያህል በዘረ መል ምህንድስና ከተሻሻሉት ትንኞችና የተፈጥሮ ትንኞች ቢዳቀሉ የሚፈጠሩት ትንኞችና ፀረ ተባይን የሚቋቋሙ ትንኞች መሆናቸው ከሚያነሷቸው ስጋቶች መካከል ይገኙበታል።
ይህንን የሚቃወሙ ሰዎችም ተግባራዊ መሆን የለበትም በሚልም 240 ሺህ ፊርማን አሳባስበዋል።
ሆኖም ፕሮጅክቱን የሰራው በእንግሊዝ ተቀማጭነቱን ያደረገው ኦክዚቴክ ኩባንያም ለአከባቢም ሆነ ለሰው ልጅ ምንም አይነት የጎንዮሽ ጉዳት የለውም፤ ፕሮጀክቱም ሲጀመር በመንግሥት ድጋፍ የተደረገባቸውን በርካታ ጥናቶች ተከናውነዋልም ብሏል።
ትንኞቹም በሚቀጥለው አመት ለሁለት አመታት በሚፈጅ ጊዜ በፍሎሪዳና አቅራቢያው ባሉ ደሴቶች ይለቀቃሉ ተብሏል።
በዚሁ አመት ግንቦት ወር የአሜሪካ አካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ ለኦክዚቴክ ኩባንያ 'አደስ አጀብቲ' የሚል መጠሪያ ያላቸውን ትንኞችን በዘረ መል ምህንድስና እንዲያሻሽላቸው ፈቃድ የሰጠው።
አደስ አጀብቲ የተባሉት ትንኞች የወባ በሽታን ጨምሮ፣ ዚካ፣ ደንጊ፣ ቺኩንጉንያን የመሳሰሉ አደገኛ በሽታዎችን በማስተላለፍ ይታወቃሉ።
እነዚህን በሽታ የሚያስተላልፉት ሴት ትንኞች የሰውን ልጅ በመንደፍ ሲሆን እንቁላል ለማምረት ደም ስለሚያስፈልጋቸው ነው።
እቅዱም ወንድ ትንኞችን በዘር መል ምህንድስና በማሻሸል ከሴት ትንኞች ጋር እንዲራቡ ማስቻል ነው።
ሆኖም ወንድ ትንኞች ፅንሱ ከማደጉ በፊት በእንጭጩ የሚገድል ፕሮቲን ያመርታሉ።
ሆነም ቀረም የነዚህን ትንኞች ቁጥር በመቀነስ ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን መግታት ነው።
ኦክዚቴክ በድረገፁ እንዳሰፈረው በብራዚል ባካሄዱት ሙከራ አመርቂ ውጤት ማሳየታቸውን ነው።