ጥቁር ቆዳ ውበት ነው ካልን ለምን ፈጣሪ ቀይ እንዲያደርገን እንጸልያለን?

የቆዳ ማቅላትን የሚያበረታታ ማስታወቂያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጥቁር መሆን ውበት ነው የምንለው እውነት ነው ወይስ ስናስመስል?

‹ከለሪዝም› ይሉታል እነሱ፡፡ እኔ ለዚህ ጽሑፍ መግባቢያነት ‹‹የቅላት ዘረኝነት›› እንድለው ፍቀዱልኝ፡፡

በአንድ ኅብረተሰብ ውስጥ ቆዳው ‹ፈካ፣ቀላ፣ነጣ› ላለ ሰው የሚሰጥ ሻል ያለ ቦታ ነው የቅላት ረዘኝነት፡፡ ለዚያ ሰው የሚሰጠው ከፍታ እንዴት ይለገጻል? በብዙ መልኩ፡፡ በአመለካከት ብቻ አይምሰላችሁ፡፡ ሁለመና ነው ነገሩ፡፡ ዕድል፣ ሥራ፣ መወደድ፣ ቁንጅና፣ ቅቡልና ወዘተ…፡፡

ጠቆር የምትል ሴት ስትወለድ፣ ‹‹አይ…! ይሁን መቼስ ምን ይደረጋል?›› የሚል ማኅበረሰብ፣ የቅላት ዘረኝነት ተጠቂ ነው፡፡ ቢያስተባብለውም፣ ባያስተባብለውም፡፡

አብዛኛው የዓለም ማኅበረሰብ በዚህ ‹የቅላት ዘረኝነት› የተበከለ ነው፡፡

ለምሳሌ ሐርሻሪን እንስማት፡፡

ኒው ዚላንድ ነበር የምትኖረው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ሕንድን ስትጎበኝ ደነገጠች፡፡ ሕዝቡ በሙሉ ቆዳውን ፈቅፍቆ ቢያነጣው ደስ የሚለው ዓይነት ነው፡፡

ሐርሻሪን ቤተሰቦቿ ከሕንድ ናቸው፡፡ እዚያ በሄደችበት የምታየውን ማመን ነው ያቃታት፡፡ ከኒው ዚላንድ ወጥታ አታውቅም ነበር ከዚያ በፊት፡፡ ለዚያ ይሆናል የደነገጠችው፡፡

በሕንድ የጎዳና ላይ ግዙፍ የደጅ ማስታወቂያዎች (ቢልቦርዶች) በብዛት አገልግሎት ላይ ይውላሉ፡፡ ብዙዎቹ መጪዎቹን አዳዲስ ፊልሞች የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ ሁሉም ላይ በቆዳ ቀለም ፈካ ያለች የአንዲት ሴት ምሥል ይታያል፡፡

ቦሊዉድ ጥቁር ቆዳ ያላት ሴት ድርሽ እንዳትል የተባለ ነው የሚመስለው፡፡

ከደጅ ቤት ስትገባ ነገሩ ባሰባት፡፡ ቴሌቪዥኑን የሞሉት ቀላ ያሉ ሕንዳዊያን ናቸው፡፡ ማስታወቂያውን የሚሠሩት ቀላ ያሉ ሕንዳዊያን ናቸው፡፡ ድራማው፣ ዜና አንባቢዎቹ፣ ተዋኞቹ፣ የመርሀግብር አጋፋሪዎቹ…በሙሉ ቅላት፣ንጣት፣ ፍካት…ይታይባቸዋል፡፡

ፍካት ስንል ራሱ አዎንታዊ ነው፡፡ ተቃራኒው መጠየም፣ መክሰል፣ መደብዘዝ ነው፡፡ ሁሉም አሉታዊ ይመስላሉ፡፡ እኛ ራሱ ስለ ከለሪዝም እያወራን፣ ራሳችን ዘረኞች ሆነን አረፍነው?

ዘረኛ የቅባት ማስታወቂያዎች

የቆዳ ቅባት ማስታወቂያው ሁሉ አንድ አይነት ይዘት ያለው መልእክት ይለፍፋል፡፡

‹‹ቆዳችሁን የሚያፈካ…ቅባት›› በሚል ተመሳሳይ ሐረግ የማይደመደም ማስታወቂያ በአገሩ ጠፋ፡፡

እንዲያውም አንደኛው ማስታወቂያ ቃል በቃል እንዲህ ይላል፡- "ሴቶች ጥሩ ባል፣ ጥሩ ሥራና የተሟላ ደስታን እንዲያገኙ ቆዳቸውን የሚያፈካ ቅባት ይጠቀሙ"

ማስታወቂያው ይህን የሚሰብከው ያለምንም ሀፍረት ነው፡፡ አድማጩም፣ ተመልካቹም ‹ታዲያ ይሄ ምን ቸግር አለው?› ይላችኋል፡፡

ችግርማ አለው፡፡ ችግሩ ዘረኛ መሆኑ ነው፡፡ ችግሩ ችግር መሆኑን እስክንረሳ መሰበካችን ነው፡፡

‹‹በዓለም ግዙፎቹ ቆዳ አምራቾቹ ጋርኒየር (Garnier) እና ሎሪያል (L'Oreal) በኒው ዚላንድም አሉ፡፡ እኔ ግን አንድም ቀን እንዲህ ብለው ምርታቸውን ሲያስተዋውቁ አይቼ፣ ሰምቼ አላውቅም፡፡ ›› ትላለች ሐርሻሪን፡፡

ሐርሻሪን ‹‹የሕንድ ፌሚኒስቷ ገጽ›› የሚል ኢኒስታግራም አላት፡፡ በዚያ በኩል ‹‹የቅላት ዘረኝነበት››ን ለመታገል ትተጋለች፡፡

የጆርጅ ፍሎይድን በሚኔሶታ መገደል ተከትሎ ተጋግሎ በነበረው የጥቁሮች እንቅስቃሴ የተነሳ በሰኔ 2020 ዓ.ም ላይ እነዚህ ግዙፍ ኩባንያዎች ምርቶቻቸው ላይ ‹‹ቀይ ቆዳ እንዲኖርሽ…›› የሚሉ ዘረኛ ሐረጎችን ከማስታወቂያቸው ለማንሳት ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡ ይህንንም በከፊል አድርገውታል፡፡ ሆኖም አስተሳሰብ በአንድ የማስታወቂያ ሐረግ መነሳት በአንድ ጀምበር ይፋቃል እንዴ? አይፋቅም፡፡ ስለዚህ የቅላት ዘረኝነት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ጋርኒየር አብዛኛዎቹን ምርቶቹን የሚሸጠው በኢሲያ አህጉር ነው፡፡ ምርቶቹን የሚታወቁት ቆዳን በማፍካት ነው፡፡

ይህ ‹‹የቅላት ዘረኝበት›› በኢሲያ አገሮች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ጉዳዬ የሚለው አልነበረም፡፡ ነውርም ሆኖ የሚታየው ሰው አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ በቃ ቀይ ሴት፣ ከጥቁር ሴት አንጻር ውብ ናት፣ ውብ ናት፤ አለቀ ፣ደቀቀ፡፡ ጥቁር ሴት ደግሞ ‹‹መቼስ ምን ይደረጋል…እግዚአብሔር ካመጣው…›› ነገር፡፡

የቆዳ ማቅላትን የሚያበረታታ ማስታወቂያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለምን ጠቆርኩ ብሎ ራስን ማጥፋት

የቅላት ዘረኝነት በአንድ ኅብረተሰብ ውስጥ ሲፀርስ ውጤቱ አደገኛ ነው፡፡ ሕጻናት ቆዳቸው ሲጠቁር አካል ጉዳተኛ እንደሆኑ ያስባሉ፡፡ ፈጣሪ የረገማቸው ይመስላቸዋል፡፡ ገና ታች ክፍል እያሉ ከእናታቸው የሚያቀላ ቅባት ሰርቀው ተደብቀው እየተቀቡ በእኩዮቻቸው ዘንድ ቅቡልነት ለማግኘት ይተጋሉ፡፡ ምክንያቱም ከቴሌቪዥኑ የሚማሩት ይህንኑ በመሆኑ።

ይህ በኢሲያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ አገራትም የሚታይ ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ጸሎታቸው ‹አምላኬ ሰው በልኬ›፣ ከሚለው ቀጥሎ ‹አምላኬ ቆዳየን ትንሽ አንጣልኝ› የሚል ሆኗል፡፡

ከላይ የሚታየው የቢልቦርድ ምስል በአይቬሪኮስት የተሰቀለ ነው፡፡ ይህንኑ የሚመሰክር፡፡

ቀድሞ ጭራሽ አጀንዳ እንኳን ያልነበረው ይህ ‹የቅላት ዘረኝነት› አሁን ብዙዎች እንዲያወሩበት ሆኗል፡፡ ይህ የኅብረተሰብ መንቃት የተፈጠረው በአጋጣሚ ነው፡፡ ወይም አይደለም፡፡

የጆርጅ ፍሎይድ ሞት ብዙ የቀለም ጉዳዮች ወደ ሚዲያ እንዲመጡ ማድረጉ ግን እሙን ነው፡፡ ማኅበራዊ የትስስር መድረኩ ክርክሩን አጧጧፈው፡፡ አሁን አሁን ጥቁር ቆዳ ያላቸው ሰዎች በቅባትም ሆነ በሽቦ ቆዳቸውን መፈተግ እንደሌለባቸው እያሰቡ መጥተዋል፡፡ ተፈጥሮ የሰጠቻቸው ቆዳ ችግር እንደሌለበት እየተገለጠላቸው ነው፡፡

የሕዝብ ንቃት ሁልጊዜም ለለውጥ ወሳኝ ነው፡፡ ለምሳሌ ለስንትና ስንት ዓመታት በገበያ የቆየው ዩኒሊቨር (Unilever) ለምሳሌ እነዚህን የቅላት ዘረኝነት የሚደግፉ ምርቶቹን ‹‹አይለመደኝም›› ብሎ ማስታወቂያውን በዚያ መንገድ ማስነገር አቁሟል፡፡

ምርቶቹንም ስማቸውን ለመቀየር ተገዷል፡፡ ለምሳሌ ፍካት (fairness), ንጣት (whitening)፣ ድምቀትና ቅላት (lightening) የሚሉትን ስሞች አስወግዷል፡፡

ፌየር ኤንድ ላቭሊ (Fair & Lovely) ሚሊዮን ዶላሮችን የሚያስገባት ምርቱ ነበር፡፡ ስሙን ቀይሮታል፡፡ ግሎው ኤንድ ላቭሊ (Glow & Lovely) በሚል፡፡ ስሙ አልሸሹም ዞር አሉ ቢመስልም አንድ አበረታች እርምጃ ሆኖ ሊወሰድለት ይችላል፡፡

ዩኒሊቨር በነዚህ ምርቶቹ እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር ትርፍ ያፍስባቸዋል፡፡

በቬርሞንት ዩኒቨርስቲ የሶሲዮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ኒኪ ካና የስም ለውጡ አሁንም የቅላትን በጎነት የሚሰብክ እንደሆነ ያሰምሩበታል፡፡ እጅግ ገናና ምርት ስለሆነ የስም ለውጥ ለማድረግ መጨከኑ በራሱ የሚደነቅ ሆኖ የትርጉም ለውጡ ግን አይታየኝም›› ይላሉ፡፡

ለዓመታት ደንበኞቻቸው ፊታቸውን ማቅላት የሚሹ ሰዎች ሆነው ቆይተዋል፡፡ ድምቀት (Glow) የሚለው ቃል የተሳሰረው ከቅላት ጋር ነው፡፡ ስለዚህ ማድረግ ያለባቸው የምርቱን ስም መቀየር ሳይሆን ምርቱን ከገበያ እስከናካቴው ማስወደግ ነበር ባይ ናቸው ፕሮፌሰሩ፡፡

የመቅላት አባዜ ምን ይዞ ይመጣል?

ጥናቶች ብዙ ተሰርተዋል፡፡ የመቅላት ዘረኝነትና የመቅላት አባዜ ዙርያ፡፡

ዋንኛው የጥናቱ ውጤት የአእምሮ ጤና ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በኢሲያዊና በአፍሪካዊ ሴቶች የተደረገ አንድ ሰፊና ጥልቅ ጥናት ‹‹ድብታ ውስጥ የመግባት እና የአእምሮ ጤና መቃወስ የቆዳ ቀለምን በጸጋ ካለመቀበል ጋር ተሳስሮ ታይቷል፡፡

በአንዳንድ ውስን አጋጣሚዎች ደግሞ ለቆዳ ቀለም መጠየም ጋር ተያይዞ በሚፈጠር ያለመፈለግ ስሜት፣ ዋጋ የማጣት ስሜት፣ የራስ ዋጋቸውን አውርደው፣ ዋጋቸውን ብቻ ሳይሆን ራሳቸውን የሚፈጠፍጡም አልጠፉም፡፡ ‹ኅብረተሰብ የማይፈልገኝ ከሆነ ለምን እኖራለሁ› ነው ነገሩ፡፡

በኔትፍሊክስ የሚታየው አንድ ተከታታይ የሪያሊቲ አውደ ትእይንት ትኩስ ክርክር ፈጥሯል፡፡ ትእይንቱ ‹‹ኢንዲያን ማችሜኪን›› ይባላል፡፡ የትእይንቱ አሰናጅ የፍቅር ጓደኛ ማደን ነው ሥራዋ፡፡ በትእይንቱ የምታገናኛቸው፣ የምትመርጣቸው በሙሉ ፈካ ያለ ቀለም ያላቸው ወንዶችና ሴቶች መሆናቸው ለጦፈ ክርክር ምክንያት ሆኗል፡፡

ቀደም ባለው ጊዜ እንዲህ ዓይነቱ ነገር እንደ ትክክል የሚቀበል ማኅበረሰብ አሁን ‹‹ግን ለምን?›› ማለት ጀምሯል፡፡ ጥቁር ሴትስ? ጥቁር ወንድስ? ጠቆር ማለት መጉደል ነው? መበደል ነው? ክፉ እጣ ነው? ማን ነው ያለው?

ደግነቱ ኅብረተሰቡ አይደለም ካለ መሆኑ ያበቃል፡፡