ካፒታሊዝም፡ የአፕል ኩባንያ ሀብት ዋጋ ግምት ሁለት ትሪሊዮን ዶላር ደረሰ

የቴክኖሎጂው ኩባንያ አፕል በስቶክ ገበያ የሀብት ምጣኔ ግምት ከቢሊዮን ዶላሮች አልፎ በትሪሊዮን ዶላር የተገመተ ሁለተኛው የዓለም ኩባንያ ሆኗል፡፡

በአሜሪካ በ2 ትሪሊዮን ዶላር የሚገመት ሀብት ያለው ኩባንያ የለም፡፡ አፕል የመጀመርያው ሆኗል፡፡

ከዚህ ቀደምም አንድ ትሪሊዮን ዶላር ለመድረስ የመጀመርያው ሆኗል፤ በ2018 ዓ.ም መጀመርያ፡፡

አሁን የአፕል የአንድ ሼር ዋጋ ግምቱ $467.77 ዶላር ደርሷል፡፡ ትናንትና ረቡዕ በነበረው የስቶክ ገበያ የኩባንያው ጥቅል ሀብት 2ሚሊዮን ዶላር መድረሱ ተበስሯል፡፡

በዓለም ላይ 2 ትሪሊዮን ዶላር ጣሪያ ለመድረስ ብቸኛና የመጀመርያ የነበረው ኩባንያ የሳኡዲ አረቢያው የነዳጅ ድርጅት አራምኮ ነው፡፡

ሆኖም አራምኮ በስቶክ ገበያ የነበረው ዋጋ ባለፈው ታኅሣሥ ወር የነዳጅ ዋጋ ማሽቆልቆልን ተከትሎ የሼር ምጣኔውም በዚያው ወርዷል፡፡ ከዚያ ወዲያ የስቶክ ዋጋ ግምቱ 1.8 ትሪሊዮን ዶላር ላይ ተቀምጧል፡፡

በሐምሌ ወር አፕል አራምኮን በመብለጥ የዓለም እጅግ ሀብታሙ ድርጅት ሆኗል፡፡.በስቶክ ገበያም በጣም ተፈላጊ የግብይይት ኩባንያ በመሆን አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል፡፡

የማያባራ ገበያ

የአይፎን ስልኮችን ፈብራኪው አፕል በዚህ ዓመት የሼር ድርሻው በ 50% ነው የተመነደገው፡፡ ይህ የሆነው ታዲያ ዓለም በኮሮና ተህዋሲ በሚታመስበት ወቅት ነው፡፡

የኮቪድ መከሰት አፕል በኢሲያ በተለይም በቻይና ያሉ መደብሮቹን እንዲዘጋ አስገድዶታል፡፡ ቻይና በድርጅቱ ላይ ፖለቲካዊ ጫና ስታደርስ ነው የቆየችው፡፡

እንዲያም ሆኖ ነው የድርጅቱ የስቶክ ድርሻ ገበያው እየደመቀለት የሄደው፡፡

ብዙዎቹ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ከሌሎች ዘርፎች በተሻለ አስቸጋሪውን ጊዜ ለማለፍ የሚችሉበት አጋጣሚ የተፈጠረ ይመስላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የስቶክ ድርሻቸው እየተመነደጉ ያሉት ከቴክኖሎጂ ጋር የተሳሰሩት ኩባንያዎች ናቸው፡፡

አፕል በዚህ የዓመቱ ሦስተኛው ምዕራፍ ላይ ማለትም ሐምሌ መጨረሻ ላይ ትርፉ ወደ 60 ቢሊዮን ዶላር መጠጋቱን አብስሯል፡፡

በአሜሪካ ከአፕል ቀጥሎ ከፍተኛ የስቶክ ግምት ዋጋ ያለው ኩባንያ አማዞን ሲሆን ምጣኔውም 1.7 ትሪሊዮን ዶላር ነው፡፡.