ደላላ፡ ሚሊየነር የሆኑ ‹‹ኢንተርናሽናል የበይነ መረብ› አጭበርባሪ ደላሎች

ጋብሬል ቤልትረን ከኡራጓይ ወደ ማያሚ የመጣው እውቅ የከበሮ ተጫዋች ለመሆን ነበር፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት የቤት ኪራይ መክፈል አይችልም ነበር፡፡

ተማሪ ከነበረችው ሴት ጓደኛው የምሳ ይበደርም ነበር፡፡ ከዚያ በድንገት ተተኮሰ፡፡ 20 ሚሊዮን ዶላር አገኘ፡፡

ነገሩ በበይነመረብ ንግድ ውስጥ በዕቃ አቅራቢና በደንበኛ መሀል የሚደረግ የድለላ ሥራ ነው፡፡

‹‹ድሮፕሺፒንግ›› ይባላል፡፡ ድለላ ለማለት እንኳ ይከብዳል፡፡ ሥራው እንዴት ነው የሚሰራው የሚለውን ቆየት ብለን እንመለስበታለን፡፡ በርካታ ሰዎች ይህንን ትርፉ የሚያቋምጥ ሥራ በመሥራት ላይ ናቸው፡፡

ለዚህ ሥራ የሚያስልገው ቆንጆ ኢንተርኔትና ቆንጆ ላፕቶብ ብቻ ነው፡፡ ጠዋት ከብርድልብስ ሳይወጡ መሰራት ይችላል ይላሉ፣ ትርፍ ያጋበሱበት፡፡

እንዴት?

ሻጮቹ እንዲያውም የሚሸጡትን ዕቃ አይዳስሱትም አይነኩትም፡፡ መጋዘን የላቸውም፡፡ ግን እየሸጡ ያተርፉበታል፡፡ ሂደቱ እንዴት እንደሆነ እንመልከት፡፡

ይሄ የበይነ መረብ ደላላ (dropshipper) ላፕቶፑን ይከፍትና ርካሽ የሆነ ዕቃ ከአንዱ የቻይና በይነመረብ ገበያ ይፈልጋል፡፡ ከዚያ ይኼ ደላላ ምን ያደርጋል? በቅመም ያበደ ሻይ እንደሚባለው በቀለም ያሸበረቀ ድረ ገጽ ያሰራና ይህንን ርካሽ ዕቃ በድረ ገጹ ይለጥፈዋል፡፡

ድረ ገጹ ግን ምርቱ 'ኦሪጅናሌ' አሜሪካ ሰራሽ ወይም ጀርመን ሰራሽ ሆኖ ነው የሚለጠፈው፡፡ ከዚያ ይኸው የበይነመረብ ደላላ ወደ ማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ይሄድና ከፍሎ 'ያበደ' ማስታወቂያ ለዚህ እቃ ያሰራል፡፡

በፌስቡክ፣ ቴሌግራም ወይም ኢንስታግራም እጅግ ተጽእኖ ፈጣሪ ለሚባሉ ሰዎች ገንዘብ እየከፈለ ይህንን ምርት ያስተዋውቃል፡፡ ይህን የሚያደርገው ምርቱ ላይ ጥርጣሬ እንዳይፈጠር በማለም ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ደንበኛ ይህንን ዕቃ በሚያዝበት ጊዜ ከገዥው መጀመሪያ ገንዘቡን ይቀበላል፡፡ ደላላው ከገዢው ገንዘቡ ሲደርሰው ነው ምርቱን ከቻይና የሚገዛው፡፡

ከዚያ ዕቃው በቀጥታ ወደ ገዢው ይጫናል፤ ከቻይና፡፡ የበይነ መረቡ ደላላ ዕቃውን አልነካውም፣ አልዳሰሰውም፡፡ ነገር ግን ገንዘብ ያገኛል፡፡ በሌላ ቋንቋ ይህ ደላላ በመንፈስ በገዥና በሻጭ መሀል ያለ ሰው ነው፡፡ የሚደንቀው ታዲያ ይህ ሥራ ወንጀል አለመሆኑ ነው፡፡ ምኑ ነው ወንጀል፡፡

ምናልባት ከሚገባው በላይ አዳንቆና አዳምቆ ማስታወቂያ መሥራት? ችግሩ በዚህ ሕጋዊ ሥራ ውስጥ የሚጨበጥ ነገር ስለሌለ አጭበርባሪዎች መኖራቸው ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደንበኞች ገንዘብ ከፍለው እቃቸው ግን አይላክላቸውም፡፡

ይህ በሕጋዊዎቹ የበይነ መረብ ደላሎች ዘንድ የሚፈጸም ሳይሆን በነሱ ስም የሚፈጸም ወንጀል ስለሆነ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ጋብሬል በዚህ መንገድ ቻይና ስሪት የሆኑ የብሔራዊ አሜሪካ እግር ኳስ ሊግ (NFL) ምርቶችን ይቸበችባል፡፡

ሰዎች የሚገዙት የአሜሪካ ኦሪጅናሌ ምርት እየመሰላቸው ነው፡፡ በዚህ መንገድ በአንድ ወር $50,000 ዶላር አተረፈ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የተጭበረበረ እቃ ሸጬ አላውቅም ይላል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች አንድ ጊዜ ጥሩ ገንዘብ ካገኙ በኋላ ይሰወራሉ፡፡

በወር ውስጥ ጥሩ ትርፍ ካገኙ በኋላ እቃ መላክ የሚያቆሙ ደላሎችም አሉ ብሏል ለቢቢሲ። አንዳንድ ጊዜ እቃዎቹ የተባሉት አይነቶች ይሆኑና ነገር ግን የአእምሮ ጥበቃ መብታቸው በማይጠበቅበት አገር ይመረታሉ፡፡ እነሱን ስንሸጥ ገንዘብ እናገኛለን፡፡

አንዳንድ ጊዜ ምርቶቹ የሌላ ሆነው ማሸጊያቸው የታዋቂ ድርጅት ስም ሊለጠፍበት ይችላል፡፡ ኬቨን ዴቪድ ሌላኛው የበይነ መረብ ደላላ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት የተጭበረበረ ነገር ውስጥ ገብቼ አላውቅም ይላል፡፡ ሆኖም ጓደኞቹ ተመሳስለው የተሰሩ ምርቶችን በመሸጥ በመቶ ሺህ ዶላሮች አጋብሰዋል፡፡

በተለይ የአፕል ገመድ አልባ የጆሮ ማዳመጫዎች AirPods ተቸብችበዋል ይለል፡፡ ሐሳዊ ምርቶች ድሮፕሺፒንግ ለበይነመረብ ንግድ አዲስ ሐሳብ አይደለም፡፡ አሁን አዲስ ያደረገው ማኅበራዊ ሚዲያው ነው፡፡ እነዚህ ደላሎች የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪዎችን ስለሚጠቀሙ በቀላሉ የተትረፈረፈ ገበያ ማግኘት ችለዋል፡፡ ለዚህም ነው ትርፋቸው አስደንጋጭ የሆነው፡፡

ቀደም ብሎ እነዚህ ሰዎች ያልዳሰሱትን ምርታቸውን ያስተዋውቁ የነበረው በኢቤይ ወይም በተለመዱ መገናኛ ዘዴዎች ነበር፡፡ አሁን ነገሩ ሁሉ ተቀየረ፡፡ ሰፊ ተቀባይነት ያገኙ የማኅበራዊ ሚዲያ ዝነኞች ምርት አስተዋዋቂ ከሆኑ በኋላ ገበያው ደርቷል፡፡

ሳራ መባርኪ ማግኔቲክ ኤስ ኤል ለሚባል ድሮፕሺፒንግ ድርጅት ውስጥ ሰርታለች፡፡ ይህ ድርጅት የሚሸጠው የራሱን ብራንድ ነው፡፡ ሆኖም ስለ ድሮፕሾፒንግ አስገራሚ ሚስጥሮችን ታውቃለች፡፡

ሳራ ለቢቢሲ ክሊክ እንደገለጸችው የዝነኞቹ የካርዳሺያን ቤተሰብ የሆነችው ኮርተኒ ካርዳሺያን ይህንን ምርት በኢኒስታግረም አስተዋወቀችው፡፡ ኮርተኒ ካርዳሺያን በኢኒስታግራም 100 ሚሊዮን ተከታይ አላት፡፡ ይህን የተጭበረበረ የውበት ምርት ለማስተዋወቅ ሁለት መቶ ሺህ ዶላር ተከፈላት፡፡

የተከፈላት ብዙ ቢመስልም ድርጅቱን ትርፍ በትርፍ አደረገችው፡፡ በገበያ ጎርፍ ተመታ፡፡ በተጽእኖ ፈጣሪዎች ማስተዋወቅ በአንድ ጊዜ እጅግ ዝነኛ ብራንድ (የንግድ መታወቂያ) ለማግኘት አቋራጭ መንገድ ሆኗል፡፡

ሳራ እንዲህ ትላለች፡- ብዙ ሰዎች እንደ ኮርተኒ ካርዳሺያን ያለ ከፍተኛ ዝና ያለው ሰው ምርትን እንዲያስተዋውቅ ምርቱ የግድ ኦርጂናሌና ያልተጭበረበረ መሆን እንዳለበት ያስባል፡፡ ያ ውሸት ነው፡፡ አንዳንድ እውቅ ሰዎች ብቻ ናቸው ሐሳዊ ምርት አስተዋውቁልን ሲባሉ እምቢ የሚሉት፡፡ ብዙዎቹ ችግር የለባቸውም፡፡