ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ግብጽ ቲክ-ቶክ 'ቀብጣችኋል' ብላ ያሰረቻቸውን ሴቶች እንድትፈታ ተጠየቀ
ግብጽ በቲክ-ቶክ 'ቀብጣችኋል' ብላ ያሰረቻቸውን ሴቶች እንድትፈታ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች ጫና እየፈጠሩ ነው፡፡
ቲክ-ቶክ በተሰኘው የማኅበራዊ ድራምባ መተግበሪያ ‹‹ቀብጣችኋል›› ያለቻቸውን ሴት የቲክቶክ ዝነኞችን በማሰሯ ነው በግብጽ ላይ ጫናው የበረታው፡፡
ሴት ልጆቹ በቲክ-ቶክ በኩል ፖለቲካዊ ተቃውሞ በማሰማታቸው አይደለም የተሳረቱት፡፡ ‹‹የግብጽን ቤተሰባዊ እሴት የሚንድ…›› ተግባር ፈጽማችኋል ተብለው ነው፡፡
ሴቶቹ በቲክ-ቶክ በቄንጠኛ ልብሶች አጊጠው ሲደንሱ ነው የሚታዩት፡፡ ከነሱ ውስጥ አምስቱ እያንዳንዳቸው ሁለት ዓመት ተፈርዶባቸዋል፡፡ ‹‹ደንግጠናል፣ እህቴ ምንም መጥፎ ነገር አልሰራችም፡፡ ወንጀለኛ አይደለችም፡፡ መታወቅ ፈልጋ ነው ቲክቶክ ላይ የወጣችው›› ብላለች ራህዋ የምትባል የታሳሪ እህት፡፡
እህቷ ማዋዳ በቲክቶክ ቀብጠሻል ተብላ ሁለት ዓመት እስር ተከናንባለች፡፡ ማዋዳ 22 ዓመቷ ሲሆን የዩኒቨርስቲ ተማሪ ናት፡፡ የግብጽን ቤተሰባዊ እሴት ንደሻል በሚል ነው እስር ቤት የተወረወረችው፡፡
ባለፈው ግንቦት ወር ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ሳያውላት በፊት በአንድ ሙዚቃ ስትደንስ የሚታይ ቪዲዮ ለቃ ነበር፤ በቲክቶክ፡፡ ወንጀሏም ይኸው ነው፡፡ እህቷ ራህዋ እንደምትለው ‹‹እናታችን እንቅልፍ አጥታለች፣ በቀን በቀን እንዳለቀሰች ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሌሊት እየተነሳች ጭምር ልጄን! ትለለች፡፡››
አምስቱ የቲክቶክ ከዋክብት በግብጽ መነጋገርያ ከሆነ ሰንብቷል፡፡ ከመዋዳ ሌላ አራት ሴቶች በግብጽ በቲክቶክ ምክንያት ዝናን የተቀዳጁ ሴቶች ናቸው፡፡ ሁሉም ሁለት ዓመት እስርና 20ሺህ ዶላር ቅጣት ተጥሎባቸዋል፡፡
ታሳሪዋ መዋዳ በቲክቶክ ዝና እያገኘች ስትመጣ ለታወቁ የልብስ አምራቾች ማስተዋወቅ ጀምራ ነበር፡፡ ጉጉቷም እውቅ ተዋናይ ለመሆን ነበር፡፡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንዳለው ደግሞ አቃቢ ሕግ ይቺን ወጣት ለመክሰስ 17 ፎቶዎችን ለፍርድ ቤት አቅርቧል፡፡
ይህም ‹ጨዋ› አለመሆኗን ለማስመስከር የተደረገ ጥረት ነው፡፡ እህቷ ራህዋ እንደተናገረችው ደግሞ እነዚህ ፎቶዎች ስልኳ ከተሰረቀ በኋላ ተገኙ የተባሉ ናቸው፡፡ ማዋዳ በመጪው ሳምንት ነሐሴ 17 ይግባኝ ትላለች፡፡
ምናልባት ፍርዱ ወደ አንድ ዓመት ዝቅ ይደረግላታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እህቷ ለቢቢሲ እንተናገረችው ‹‹በርካታ ተዋንያን እንደ እህቴ ለብሰው በቴሌቪዥን ይታያሉ ማንም ምንም ብሏቸው ግን አያውቅም፡፡›› መዋዳ ፍርድ ቤት ቀርባ ዳኛው ቅጣቱን ሲያነቡላት ራሷን ስታ መውደቋ ተዘግቧል፡፡