ናይጄሪያ፡ ለአመታት በቤተሰቦቹ ጋራዥ ውስጥ ተቆልፎበት የነበረው ናይጄሪያዊ ነፃ ወጣ

ከወገቡ በታች እርቃኑን ሆኖ ያለ ድጋፍ መንቀሳቀስ የማይችል ሆኖ ነው ፖሊስ ያገኘው።

ናይጀሪያዊው ግለሰብ በቤተሰቦቹ ጋራዥ ውስጥ ለሶስት አመታት ያህል ተቆልፎበት ነበር ብሏል ፖሊስ።

በሰሜናዊዋ ናይጄሪያ ካኖ ከተማ በሚገኝ ጋራዥ የቆለፉበት ቤተሰቦቹ ናቸው።

የ32 አመቱ አህመድ አሚኑ የተገኘው ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ ነው።

ጥርጣሬ ያደረባቸው ጎረቤቶቹ ሂውማን ራይትስ ኔትወርክ የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅትን ስለ አህመድ ሁኔታ ያሳውቃሉ።

አንዳንድ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ለሰባት አመታትም ያህል ተቆልፎበት እንደነበር ነው።

አህመድ ነፃ በወጣበት ወቅት የተቀረፀ ቪዲዮ እንደሚያሳየው በከፍተኛ ሁኔታ የገረጣ፣ አጥንቱ የገጠጠና የተጎሳቆለ ሲሆን መራመድ አቅቶትም በድርጅቱ ሰራተኞችም ድጋፍ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።

ቪዲዮውም በማህበራዊ ሚዲያ የተጋራ ሲሆን አሰቃቂም ነው ተብሏል። አጥንት ብቻ የሆነው ሰውነቱም ብዙዎችን አስደንግጧል።

"አህመድን ስናገኘው በተጎሳቆለ ሁኔታ ነው። ከተቆለፈበት ጋራዥም መውጣት ስለማይችል ባለበት ቦታም ነው የሚፀዳዳው። ምግብም የሚሰጠውም አይመስልም። ሞቱን እየተጠባበቀ ያለም ነው የሚመስለው። በጣም አሰቃቂ ነው" በማለት የሂውማን ራይትስ ኔትወርክ ኃላፊ ሃሩና አያጊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአህመድ አባትና እንጀራ እናቱም በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ምርመራ እንደተከፈተባቸውም የፖሊስ ቃለ አቀባይ ሃሩና ኪያዋ በመግለጫቸው አትተዋል።

አህመድ አደንዛዥ ዕፅ ይጠቀማል በሚል ጥርጣሬ ለአመታት እንደቆለፉበት፣ አየርም አግኝቶ እንደማያውቅ ተገልጿል። ምግብም በበቂ ሁኔታ እያገኘ ስላልነበር የጤናውም ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድቷል።

በናይጄሪያ በቤተሰቦቹ ተቆልፎበት እንዲህ በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገኝ አህመድ በዚህ ሳምንት ብቻ ሁለተኛው ነው።

በዚህ ሳምንት ረቡዕ በሰሜናዊ ምዕራብ ናይጄሪያ ኬቢ ግዛት ለሁለት አመታት ያህል በእንስሳ በረት ተቆልፎበት የነበረ የአስር አመት ታዳጊ ነፃ ወጥቷል። የቆለፉበት ቤተሰቦቹ ናቸው የተባለ ሲሆን በፖሊስ እገዛም ነው የወጣው።