የቤይሩት ፍንዳታ፡ በዋና መዲናዋ ፀረ-መንግሥት ተቃውሞ ተቀሰቀሰ

ቤይሩት

የፎቶው ባለመብት, REUTERS

ሐሙስ ዕለት በሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ተቃውሞ ተቀስቅሶ ሰልፈኞች ከሃገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ጋር ተጋጭተዋል።

የፀጥታ ኃይሎች የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት አካባቢ የነበሩ ሰልፈኞችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ተጠቅመዋል።

ተቃውሞ የተቀሰቀሰው ባለፈው ማክሰኞ ቤይሩት ውስጥ ከፈረንጆቹ 2013 ጀምሮ ችላ ተብሎ ተከማችቶ የነበረ 2750 ቶን አለሙኒዬም ናይትሬት ፈንድቶ የበርካቶችን ሕይወት በመቅጠፉ ነው።

በርካታ የሊባኖስ ዜጎች ፍንዳታው በመንግሥት ቸልተኝነት አማካይነት የተከሰተ ነው ይላሉ።

በርካቶችን ባስደነገጠው ፍንዳታ ምክንያት እስካሁን ድረስ ቢያንስ 137 ሰዎች ሲሞቱ ከ5 ሺህ በላይ ሰዎች ቆስለዋል።

ፍንዳታው በዋና ከተማዋ የነበረውን አንድ ሰፈር ሙሉ በሙሉ ሲያወድም አሁንም በርካታ ሰዎች ያሉበት አይታወቅም።

የሃገሪቱ ዜና ወኪል እንደሚለው መንግሥት 16 ሰዎችን ይዞ ምርመራ እያደረገ ነው።

ከፍንዳታው በኋላ ሁለት የመንግሥት ባለሥልጣናት በገዛ ፈቃዳቸው ሥራ ለቀዋል። የሕዝብ እንደራሴው ማርዋን ሃምዴሽ ባለፈው ረቡዕ ራሳቸውን ሲያገሉነ በጆርዳን የሊባኖስ አምባሳደር የሆኑት ትሬሲ ቻሞን ደግሞ ትላንት [ሐሙስ] ውድመቱ አዲስ መንግሥት እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ ነው በማለት ሥልጣን ለቀዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ቤይሩትን ከጎበኙ በኋላ ሌባኖስ 'መሠረታዊ ለውጥ' ያስፈልጋታል ሲሉ ተናግረዋል።

አልፎም የፍንዳታው መንስዔ በዓለም አቀፍ ድርጅት እንዲጣራ ጥሪ አቅርበዋል።

ቤይሩት የሚገኘው የቢቢሲው ኩዌንቲን ሰመርቪል የወደመው ሥፍራ ሊባኖስን ከዓለም የሚያገናኝ ነበር ይላል። 80 በመቶ የሚሆነው የሃገሪቱ ገቢ የሚመነጨው ከዚህ በፍንዳታው ምክንያት ከጥቅም ውጭ ከሆነው ወደብ ነው።

"ቤይሩት ውስጥ ለአምስት ዓመታት ቆይቻለሁ። ነገር ግን አሁን ከተማዋ እንደዚህ የማላውቃት እስክትመስል ድረስ ተመሳቃቅላለች። የሚሰማው የአምቡላንስ ጩኸት ነው፤ ኦና ሕንፃ፣ ኦና መንገድ።"

"መንገድ ላይ ሁሉም ሰው መጥረጊያ በእጁ ይዞ ያፀዳል። ነገር ግን የሚዘለቅ አይደለም። እንዴት የአንዲት ከተማን ወድመት በመጥረጊያ ማፅዳት ይቻላል?" ሲል ኩዌንተን ይጠይቃል

በሕይወት የሚገኝ ሰው ይኖር ይሆን?

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በፍርስራሾች ስር በሕይወት ያሉ ሰዎች ካሉ በሚል ፍለጋቸውን ቀጥለዋል። የደህንነት ሰዎች ደግሞ አደጋው የደረሰበትን ሥፍራ ከልለው ምርመራ እያደረጉ ነው።

የፈረንሳይ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ምናልባትም በሕይወት ያሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ ይላሉ።

ከሠራተኞቹ መካከል አንዱ ለፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ሰባት ወይም ስምንት የሚሆኑ ሰዎች በአንድ ሕንፃ የአደጋ ጊዜ ክፍል ውስጥ ታፍነው ይገኛሉ፤ እነሱን ለማዳን እየጣርን ነው ሲል ነግሯቸዋል።