ከቻይና ማጎሪያ ካምፕ የተለቀቀው የሞዴሉ ምስል

ሜርዳን ጋፓር
የምስሉ መግለጫ, ሜርዳን ጋፓር

ሜርዳን ጋፓር ካሜራ ፊት ነው መቆም የለመደው።

ታዎባዎ ለተሰኘው የድረ-ገፅ ገበያ ሞዴል የሆነው የ31 ዓመቱ ሜርዳን ለወትሮው እያጌጠ ፎቶ በመነሳትና ቪድዮ በመቀረፅ ማስታወቂያ በመሥራት ነበር የሚታወቀው።

ነገር ግን አንደኛው የሞዴሉ ቪድዮ ከሌሎቹ ለየት ያለ ነበር። ከኋላው የሚታየው ያማረና የሚያብረቀርቅ ስቱድዮ ሳይሆን የቆሸሸ ግድግዳና የዛገ የብረት መስኮት ነው። ቪድዮው ላይ ሰውዬው ፊቱ ገርጥቶ፤ የቆሸሸ ልብስ ለብሶ፤ ግራ እጁ ከአልጋው ብረት ጋር በካቴና ተጠርንፎ፤ በቀኝ እጁ ካሜራውን ይዞ ይታያል።

ቢቢሲ የሜርዳን ተንቀሳቃሽ ምስል ብቻ ሳይሆን በርካታ የፅሑፍ መልዕክቶችንም አግኝቷል። ፅሑፎቹና ምስሎቹ የቻይናን ድብቅ ማጎሪያ ካምፕ ምስጢር የሚያጋልጡ ናቸው።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ቻይና ከአንድ ሚሊዮን በላይ የዩገር ብሔረሰብ አበላትን ዢንጂያንግ በተሰኘው ግዛት በሚገኝ ድብቅ ካምፕ ውስጥ ማጎሯን የሚያሳዩ መረጃዎች ወጥተዋል።

በርካታ ሺህ ሕፃናት ከወላጆቻቸው እንዲለዩ ተደርገዋል፤ ሴቶች ደግሞ በግዴታ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንዲወስዱ ተገደዋል።

የቻይና መንግሥት የዩገር ሙስሊም ብሔረሰብ አባላት ላይ ግፍ አልፈፀምኩም፤ ካምፖቹም ተዘግተዋል ቢልም የሞዴሉ ምስል በርካቶች አሁንም በማጎሪያዎች ውስጥ እንዳሉ ያሳያል።

የዢንጂያንግ ግዛት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንደ አዲስ እያገረሸባት ነው። ቢሆንም ካምፑ ውስጥ ያሉ የዩገር ብሔረሰብ አባላት አሁንም በተጨናነቀ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚኖሩት።

ቢቢሲ የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የዢንጂያንግ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ መረጃዎች ያዘለ ጥያቄ በተደጋጋሚ ቢያቀርብም ምላሽ አላገኘም።

የሞዴሉ ቤተሰቦች ከልጃቸው ድምፅ ከሰሙ ከአምስት ወር በላይ ሆኗቸዋል። ሞዴሉ የለቀቀው የ4 ደቂቃ ከ38 ሰከንድ ምስል ደግሞ የበለጠ ጫናና ቅጣት ሊያስከትልበት እንደሚችል ገምተዋል። ቢሆንም ግን የዩገር ብሔረሰብ አባላት የሚደርስባቸውን በደል ለማሳየት ስላደረገው ጥረት ያደንቁታል።

ኔዘርላንድስ የሚኖረው የሜርዳን አጎት አብዱልሃኪም ጋፓር ተንቀሳቃሽ ምስሉ ልክ እንደ ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ ቪድዮ ሕዝባዊ አመፅ ያስነሳል ብሎ ያምናል።

የዩገር ብሔረሰብ አባላት የተርኪክ ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው። ዋነኛ እምነታቸው ደግሞ እስልምና ነው። ዘራቸውም ከመካከለኛ እስያ የሚመዘዝ ነው። የብሔረሰቡ አባላት ለበርካታ ዘመናት ከቻይና መንግሥትና ከማሕበረሰቡ መገለል ሲደርስባቸው ነው የኖሩት።

ሞዴሉ ሜርዳን እዚህ ደረጃ ለመድረስ ብዙ ወጥቷል፤ ተንገላቷል። ነገር ግን ከማሕበረሰቡ የሚደርስበት መገለል መንግሥት ወገኖቹ ላይ ከሚያደርሰው ጫና ጋር ሲነፃፀር እምብዛም እንዳልሆነ ይናገር እንደነበር ቤተሰቦቹ ያስረዳሉ።

በፈረንጆቹ 2013 እና 14 ቤይጂንግና ኩሚንግ ከተማዎች ላይ ለተሰነዘረው ጥቃት የቻይና መንግሥት የዩገር ተገንጣይ ኃይል አባላትን ተጠያቂ ያደርጋል። የዩገር ብሔረሰብ አባላት ላይ ከፍተኛ ጫና መድረስ የጀመረው ከዚያ በኋላ ነው።

በ2018 ሜርዳን አደንዛዥ ዕፅ ይዘሃል ተብሎ ታሰረ። ጓደኞቹ ግን እስከዛሬም ድረስ ወንጀሉ መሠረት ቢስ ነው ይላሉ። ሞዴሉ የቻይና ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ቀርቦ የ16 ወራት እሥር ተፈረደበት። ከተፈታ ከአንድ ወር በኋላ ፖሊስ የመኖሪያ በሩን በርግዶ ገብቶ ለአስገዳጅ ሥልጠና ወደ ዢንጂያንግ መሄድ አለብህ ብሎ ወሰደው።

ቢቢሲ፤ ሞዴሉ ለሁለተኛ ጊዜ በቁጥጥር ሥር ሲውል ምንም ዓይነት ወንጀል እንዳልፈፀመ ማረጋገጥ ችሏል።

በርካታ የዩገር ብሔረሰብ አባላት ከቻይና ከተሞችም ሆኑ ከሌሎች ሃገራት በግዳጅ ተይዘው ወደ ዢንጂያንግ የሚመጡት ትምህርት እንዲወስዱ በሚል ስም ነው።

የሞዴሉ ቤተሰቦች ልጃቸው ከጠፋ ከአንድ ወር በኋላ አስደናቂ ዜና ሰሙ። ሜርዳን ስልኩን አግኝቶ ከተቀረው ዓለም ጋር መገናኘት ቻለ።

ዊቻት የተሰኘው የቻይና ማሕበራዊ ሚድያ ላይ መልዕክቱን በፅሑፍ ያሰፈረው ሜርዳን የደረሰበትን ሁሉንም ነገር ይፋ አድርጓል። በጠባብ ቤት ውስጥ እግርና እጆቻቸው አንድ ላይ የተጠፈሩ ሰዎች መመልከቱን ሳይቀር ነው የተናገረው።

ማጎሪያ ካምፖቹ በጣም ለኑሮ የማይመቹ ከመሆናቸው የተነሳ በርካታ ጊዜ ከዚህ ኑሮ ሞት እንደሚመኝም ይፋ አድርጓል። ከምርመራ ክፍል የሚወጡ አሰቃቂ ድምፆች የአእምሮ ሰላም እንደነሱትም አልሸሸገም።

ሞዴሉ የደረሰበትንና የተመለከተውን በተመለከተ ሰፋ ያለ ፅሑፍ ነው ለቻይናውያንና ለዓለም ያጋራው።

ሜርዳን አሁን ስላለበት ሁኔታ ምንም የሚታወቅ ነገር የለም። ባለሥልጣናትም ሞዴሉ የትና በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የሰጡት መረጃ የለም።

የቻይና መንግሥት አሁንም ቢሆንም የዩገር ብሔረሰብ አባላት ላይም ሆነ ሌሎች አናሳ ጎሳዎች ላይ ምንም ዓይነት ግፍ አልፈፀምኩም ሲል ያስተባብላል።