ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለ3 ቢሊዮን እንስሳት" መጥፋት" ምክንያት የሆነው የአውስትራሊያ ሰደድ እሳት
ባለፈው ዓመት በአውስትራሊያ ተከስቶ በነበረው ሰደድ እሳት 3 ቢሊየን የሚጠጉ እንስሳት ሳይሞቱ ወይም ሳይሰደዱ እንዳልቀረ ተመራማሪዎች አስታወቁ።
ይህንን ሪፖርት ያወጣው በዱር እንስሳትና በአካባቢ ጥበቃ ላይ የሚሰራው ግብረ ሰናይ ድርጅት [WWF] የጥናቱ ውጤት በዘመናዊ የዓለም ታሪክ ካጋጠሙ በጣም አስከፊው አደጋዎች አንዱ መሆኑን አመላክቷል ብሏል።
ባለፈው ዓመት የተከሰተው ይህ የሰደድ እሳት በተለያዩ አውስትራሊያ ግዛቶች ተስፋፍቶ ቢያንስ የ33 ሰዎችን ሕይወት ነጥቋል።
አጥቢ እና ተሳቢ እንስሳት፣ ወፎች እና እንቁራሪቶች በነበልባሉ ሞተዋል አሊያም ምቹ ሁኔታ በማጣት ጠፍተዋል።
የእሳት አደጋው በተስፋፋበት ጥር ወር ላይም ተመራማሪዎች በኒው ሳውዝ ዌልስ እና ቪክቶሪያ ብቻ 1.25 ቢሊየን እንስሳት እንደሞቱ ግምታቸውን አስቀምጠው ነበር።
ይሁን አንጂ አሁን አዲስ የወጣው ግምት ሌሎች ቦታዎችንም አካቷል።
ከእንግሊዝ ስፋት ጋር የሚስተካከል 11.46 ሚሊየን ሄክታር መሬትም ከመስከረም እስከ የካቲት ድረስ ባሉት ወራት ውስጥ በእሳት ወድሟል።
የሰደድ እሳቱ ያሳደረው ተፅእኖ ምን ነበር?
በአውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲዎች 10 ተመራማሪዎች የቀረበውን ፕሮጀክት የተከታተሉት ፐሮፌሰር ክሪስ ዲክማን ጉዳቱን አስመልክቶ "3 ቢሊዮን የሚጠጉ እንስሳት መጥፋታቸው ሲታሰብ በጣም ከፍተኛ ጉዳት ነው፤ ለማሰብ የሚከብድ ቁጥር ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሮፌሰሩ አክለውም በአደጋው ምን ያህል እንስሳት እንደሞቱ ትክክለኛ ቁጥሩን ማስቀመጥ ባይችሉም፤ እንስሳቱ ከእሳት ነበልባሉ የማምለጥ እና በሕይወት የመገኘት እድላቸው በምግብና በመጠለያ እጥረት ምክንያት "ያን ያህል ሰፊ አይደለም" ብለዋል።
የተገለፀው ቁጥር የተቀመጠው አደጋው ከመከሰቱ በፊት በአካባቢዎቹ ያሉ እንስሳት ቁጥርን መሰረት መሆኑን የተገለፀ ሲሆን፤ በመረጃ ውስንነት ምክንያትም የጀርባ አጥንት የሌላቸው እንስሳት በሪፖርቱ ውስጥ አልተካተቱም።
የካቲት ወር ላይ የአውስትራሊያ መንግሥት ከሰደድ እሳቱ በኋላ አስቸኳይ እርዳታ የሚፈልጉ 113 የእንስሳት ዝርያዎችን ለይቶ ነበር።
በዚህም በዝርዝሩ ውስጥ ያሉት ሁሉም ለማለት በሚያስችል መልኩ 30 በመቶ የሚሆነውን መኖሪያቸውን አጥተዋል።
ይህንንም ተከትሎ መንግሥት ለዱር እንስሳትና አካባቢ ጥበቃ 35 ሚሊየን ዶላር ለመስጠት ቃል ቢገባም የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች ግን አውስትራሊያ የአካባቢ ጥበቃ ሕጓን እንዲታጠብቅ ጠይቀዋል።
አውስትራሊያ አደጋውን አስመልክቶ ልዩ ምርመራ እያደረገች ሲሆን ውጤቱም ህዳር ላይ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በተደጋጋሚና ባልተጠበቀ መልኩ ለሚነሳው የሰደድ እሳት ምክንያቱ የአየር ንብረት ለውጥ መሆኑንም በርካታ ተመራማሪዎች እየገለፁ ነው።
ባለሙያዎቹ አክለውም ከእሳቱ ይወጣ ከነበረው ጭስ ጋር ተያይዞም ከ445 በላይ ሰዎች ሕይወት ማለፉን አስታውቀዋል።