ኤምሬትስ ለመንገደኞቹ የኮቪድ -19 ሕክምናና የቀብር ሥነ ስርዓት ወጪን እሸፍናለሁ አለ

ኤምሬትስ አየር መንገድ በወረርሽኙ ሳቢያ ከበረራ ተስተጓጉለው የነበሩ መንገደኞች ዳግም ወደ በረራ እንዲመለሱ ለማድረግ የኮቪድ -19 የነፃ መድህን ዋስትና እንደሚሰጥ አስታወቀ።

ኤምሬትስ ይህን ውሳኔ ያሳለፈ የመጀመሪያው አየር መንገድ ነው ተብሏል።

በመሆኑም መንገደኞቹ ጉዞ በሚያደርጉበት ሰዓት በኮሮናቫይረስ ከተያዙ የሕክምና ፣ የሆቴል ለይቶ መቆያ እንዲሁም ለቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ማስፈፀሚያ ወጪ እንደሚሸፍን ገልጿል።

አየር መንገዱ ይህንን ያስታወቀው ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በተደረገው እርምጃ በዓለም ላይ ያሉ አየር መንገዶች ኢኮኖሚ ክፉኛ መመታቱን ተከትሎ ነው።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የዓለማችን ትልቁ 'ሎንግ ሃውል' አየር መንገድ ከ9 ሺህ የሚበልጡ ሰራተኞቹን ሊቀንስ እንደሆነ ማስታወቁ ይታወሳል።

"አሁን ድንበሮች እንደገና እየተከፈቱ ስለሆነ ሰዎች የመብረር ፍላጎት እንዳላቸው እናውቃለን፤ ይሁን እንጂ በጉዟቸው ወቅት ያልተጠበቀ ነገር ቢከሰት ዋስትና ይፈልጋሉ" ሲሉ የኤምሬትስ ግሩፕ ኃላፊ ሼክ አሕመድ ቢን ሳኢድ አል ማክቶም በመግለጫቸው ተናግረዋል።

ድርጅቱ እንዳለው መንገደኛው ከተጓዘበት ቀን ጀምሮ ለ31 ቀናት የሚያገለግለው ዋስትናው፤ ለተጠቃሚው የሚቀርብ ሲሆን እስከ መጭው ጥቅምት ወር መጨረሻ ድረስ አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል።

የደንበኞች የጉዞ ደረጃ እና መዳረሻ የተለያየ ቢሆንም ሽፋኑ ለሁሉም መንገደኞች ነፃ ነው ተብሏል። የተለየ ምዝገባ ሳያስፈልገውም ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል።

መቀመጫውን ዱባይ ያደረገው አየር መንገድ ኢንሹራንሱ 176 ሺህ 500 ዶላር የሚሆን የሕክምና ወጪ እንደሚሸፍን ተናግሯል።

ከዚህም በተጨማሪ መንገደኞች በሆቴል ውስጥ ራሳቸውን ለ2 ሳምንታት ለይተው ለመቆየት እንዲችሉም በቀን 100 ዩሮ ወጪን ይሸፍናል።

ምን አልባት መንገደኛው በኮቪድ 19 ሳቢያ ሕይወታቸው የሚያልፍ ከሆነም የቀብር ሥነ ሥርዓት ማስፈፀሚያ የሚሆን 1 ሺህ 500 ዩሮ እንደሚሰጥ ገልጿል።

የመብረር ስጋት

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ አገራት ድንበራቸውን በመዝጋታቸው እና ተጓዦችም በጉዞ ወቅት ለበሽታው እጋለጣለሁ በሚል ስጋት በረራ በማቆማቸው የአየር ትራንስፖርት ዘርፉ ክፉኛ ተጎድቷል።

ይህ ብቻ ሳይሆን በጃፓን የሚካሄደው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች፣ የሙዚቃ ትዕይንቶች፣ የኢንዱስትሪ ስብሰባዎችን ጨምሮ ትላልቅ ክንውኖችም ተሰረዝዋል አሊያም ጊዜያቸው ተራዝሟል። ይህም በአየር ትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ተፅእኖ አሳድሯል።

ባለፈው ወር ዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር በተያዘው ዓመት ከዚህ በፊት ተመዝግቦ የማያውቅ አስከፊ የኢኮኖሚ ቀውስ እንደሚያጋጥም አስጠንቅቋል።

የግሎባል ኢንዱስትሪ ግሩፕ በበኩሉ በወረርሽኙ ሳቢያ በዚህ ዓመት አየር መንገዶች 84 ቢሊየን ዶላር ያሳጣቸዋል ብሏል፤ ከቀደመው ዓመት ጋር ሲነፃፀርም ገቢው 50 በመቶ አሽቆልቁሏል።

በዚህም ሳቢያ በርካታ አየር መንገዶች ከበረራ ውጭ እንዲሆኑና በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ሰራተኞችን ለመቀነስ ተገደዋል።

ከሦስት ሳምንታት በፊት የኤምሬትስ ፕሬዚዳንት ድርጅታቸው በወረርሽኙ ሳቢያ 9 ሺህ ሰራተኞችን ሊቀንስ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፕሬዚደንቱ ቲም ክላርክ አየር መንገዱ 10 በመቶ የሚሆነውን ሰራተኛውን የቀነሰ ቢሆንም ምን አልባት ይህ ቁጥር ወደ 15 በመቶ ከፍ ሊል ይችላል ብለዋል።

ኤምሬትስ ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት 60 ሺህ ሰራተኞች ነበሩት።

የመካከለኛው ምስራቅ አየር መንገድ - ኤምሬትስ ምን ያህል ሰራተኞችን ሊቀንስ እንደሚችል ይፋ ሲያደርግ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ተብሏል።