የቀድሞውን የአል-በሽር መንግሥት ለመገልበጥ የሞከሩ ሰዎች የጅምላ መቃብር ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እአአ 1990 ላይ የኦማር አል-በሽር መንግሥት ላይ መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ የሞከሩ ሰዎች አስክሬን በጅምላ የተቀበረበት ስፍራ ተገኘ።
በጅምላ መቃብሩ የጦር አባላት ናቸው የተባሉ የ28 ሰዎች አስክሬን ተገኝቷል።
ኦማር አል-በሽር ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ነበር ስልጣን የያዙት።
አል-በሽር ላይ የተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት ከመክሸፉ በፊት መፈንቅለ መንግሥቱን ያሴሩ የጦር አመራሮች፤ በርካታ የጦሩ ዋና መሥሪያ ቤቶችን እና የጦር ህንጻዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋል ችለው ነበር።
ይሁን እንጂ መፈንቅለ መንግሥቱ ከከሸፈ በኋላ በቁጥጥር ሥር ውለው ተገድለዋል።
የጅምላ መቃብሩ እንዴት ተገኘ?
የሰዎቹ አስክሬን የተገኘው በሱዳኗ ኦማዱረማን ከተማ ነበር።
ዐቃቢ ሕጉ ታጌለሲር አል-ቤብረ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ሲናገሩ፤ የጅምላ መቃብሩ ፍለጋ በቀድሞ የሱዳን መሪ አል-በሽር የተፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች ምርመራ አካል ነው ብለዋል።
"የጅምላ መቃብሩን ስፍራ ለማግኘት 22 ባለሙያዎች እና ሦስት ሳምንታት አስፈልገዋል" ብለዋል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ።
አል-ቤብረ ጨምረው እንደተናገሩት፤ የጅምላ መቃብሩን መቆፈር እና የሟቾቹን ማንነት የማጣራት ቀጣዩ ተግባራችን ነው ብለዋል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መሰል የጅምላ መቃብር ስፍራ ሲገኝ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
ባሳለፍነው ወር የአገሪቱ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እንዳለው፤ እአአ 1998 ላይ ከውትድርና ስልጠና ካምፕ ለማምለጥ ሲሞክሩ የተገደሉ ተማሪዎች አስክሬንን የያዘ የጅምላ መቃብር ተገኝቶ ነበር።
ባለፈው ዓመት በሕዝባዊ ተቃውሞ ከስልጣን የተባረሩት አል-በሽር ካርቱም በሚገኘው እስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ።
ኦማር አል-በሽር ላይ የሙስና ክስን ጨምሮ በርካታ ክስ ተመስርቶባቸዋል።
የ76 ዓመቱ ኦማር አል-በሽር እአአ 1989 ላይ ወደ ስልጣን ባመጣቸው መፈንቅለ መንግሥት ላይ በነበራቸው ተሳትፎ ክስ ተመስርቶባቸው ከትናንት በስቲያ በመዲናዋ ካርቱም በሚገኘው ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር።
አል-በሽር በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙ ከሆነ የሞት ፍርድ ሊበየንባቸው ይችላል ተብሏል።
አል-በሽር በሱዳኗ ዳርፉር ግዛት በተፈጸሙ የሰብአዊ መበት ጥሰቶች፣ የዘር ማጥፋት እና የጦር ወንጀሎች በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ይፈለጋሉ። የሱዳን የሽግግር መንግሥት ከወራት በፊት የቀድሞ መሪውን ለፍርድ ቤቱ አሳልፎ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን አስታውቆ ነበር።
















