በኮንሶ ዞን እና በአሌ ልዩ ወረዳ በተከሰተ ግጭት 17 ሰዎች ሲሞቱ 20 ሺህ ተፈናቀሉ

በደቡብ ክልል በኮንሶ ዞን እና በአሌ ልዩ ወረዳ መካከል በተነሳ የመሬት ይገባኛል ግጭት ቢያንስ የ17 ሰዎች ህይወት ሲጠፋ ከ21 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ለቢቢሲ ተናገሩ።

ግጭቱ የተከሰተው ከመሬት ይገባኛል ጋር ተያይዞ መሆኑን ያረጋገጡት የአሌ ልዩ ወረዳ ተጠባባቂ አስተዳዳሪ አቶ ካራ ማሞ ጥያቄው የቆየና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በሁለቱ አካባቢ አስተዳደሮች መካከል ውይይት ሲደረግ እንደነበር አስታውሰዋል።

የኮንሶ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሀሰን ወላሎ ደግሞ በአሌ ልዩ ወረዳ እና በኮንሶ ዞን ኮለኔ ክላስተር መካከል የደን መሬት እንደነበር በመናገር፣ የአሌ ልዩ ወረዳ አርሶ አደሮች ደኑን አላግባብ በመመንጠር ለመጠቀም መሞከራቸው ግጭቱ መቀስቀሱን ይናገራሉ።

ግጭቱ ከእሁድ እለት ጀምሮ የተቀሰቀሰ መሆኑን የሚናገሩት ሁለቱ ኃላፊዎች በአሌ ልዩ ወረዳ ስድስት ሰዎች በኮንሶ ዞን ደግሞ የ11 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ገልፀው፤ በልዩ ወረዳው በኩል የቆሰሉ ሰዎች ቢኖሩም መረጃው ሙሉ በሙሉ አለመጠናቀሩን አስተዳዳሪው ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በኮንሶ ዞን በኩል ግን ዘጠኝ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት እንደደረሰ አቶ ሀሰን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ግጭቱ በዋናነት የተቀሰቀሰው አሌ ልዩ ወረዳ እና ኮንሶ ዞን በሚዋሰኑበት ኮለኔ ክላስተር ቢሆንም ነገር ግን ችግሩ አሁን ወደ ሌላ አዋሳኝ አካባቢ፤ ቱሩ ክላስተር ተስፋፍቶ ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውንም አቶ ሀሰን ጨምረው አስረድተዋል።

እንደ አቶ ሀሰን ገለፃ ከሆነ በኮለኔ ክላስተር ይኖሩ የነበሩ 15 ሺህ ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ እንዲሁም በቱሩ ክላስተር ላይ ደግሞ ይኖሩ የነበሩ ከ6000 በላይ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል።

አቶ ካራ በበኩላቸው በልዩ ወረዳው አንዳንድ ቀበሌዎች ላይ በሦስትና ሁለት ዙር ቃጠሎ መድረሳቸውንና ከፍተኛ ውድመት መድረሱን በመግለጽ፣ ተሰብስቦ በማሳ ላይ የነበረ የበቆሎ ሰብል ላይ ቃጠሎ መድረሱንም ይናገራሉ።

"ማሳ ላይ ያለ የበቆሎ ሰብል ቃጠሎ እንደደረሰበት ለማወቅ ችለናል" በማለት የደረሱ ዝርዝር ጉዳቶችን አጠናቅሮ ሪፖርት ለማድረግ አሁንም አልፎ አልፎ ተኩስ ስለሚሰማ አለመቻላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በግጭቱ በኮንሶ በኩል በሁለቱ ክላስተሮች ስር ያሉ አራት መንደሮች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ቤቶች በእሳት የተቃጠሉ ሲሆን ሁለት መንደሮች ደግሞ ሙሉ በሙሉ ሁለቱ ደግሞ በከፊል መውደማቸውን አቶ ሀሰን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ግጭቱ ያልታሰበ ነበር ያሉት አቶ ሀሰን የዞኑ የፀጥታ ኃይልም ሆነ የክልሉ የፀጥታ ኃይል ለመቆጣጠር ቢሞክርም አቅጣጫ በመቀያየርና በሦስትና በአራት የተለያዩ ቦታዎች ግጭቱ በመካሄዱ ለመቆጣጠር ፈታኝ እንደሆነ ገልጸዋል።

የአሌ ልዩ ወረዳ እና በኮንሶ ዞን ተጎራባች ቀበሌዎች መካከል ያለውን ችግር በሰላማዊ ወይይት ለመፍታት የአገር ሽማግሌዎች ተሳትፈውበት በተደጋጋሚ ሙከራ መደረጉን የሚናገሩት ሁለቱ ኃላፊዎች፤ ነገር ግን መግባባት ላይ ሊደረስ አልተቻለም ይላሉ።

አሌ እና ኮንሶ ተጎራባቾች አካባቢዎች መሆናቸውን በመጥቀስም ሕዝቡ ለረዥም ጊዜ አብሮ የኖረ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

አቶ ሀሰን አክለውም ከዚህ በፊት ግጭት ሲፈጠር በአጭር ጊዜ ውስጥ ይፈታ እንደነበር በማስታወስ፣ አሁን ግን ችግሩን ከባድ ያደረገው የታጠቁ ኃይሎችና በአስተዳደር ውስጥ ያሉ አካላት በመሳተፋቸው መሆኑን በማንሳት ይከስሳሉ።

ለዚህ ምላሽ የሰጡት አቶ ካራ ማሞ በበኩላቸው፤ ገና ማጣራት ሳይደረግና በአግባቡ ምርመራ ሳይኖር መናገር ከባድ መሆኑን ጠቅሰው አሁን አካባቢውን የማረጋጋት ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን በመግለጽ ለወደፊት ተጣርቶ ተሳትፎ ያላቸው አካላትን በመለየት ሕጋዊ ርምጃ እንደሚወሰድ አረጋግጠዋል።

የፌደራልና የደቡብ ክልል የጸጥታ ኃይሎች በአካባቢዎቹ ለሰዎች ህይወትና ለንብረት መውደም ምክንያት የሆነውን ግጭት ለማስቆም ወደ አካባቢው መሰማራታቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።