ኢትዮጵያ ውስጥ ታስሯል የተባለው ኬንያዊ ጋዜጠኛ ያሲን ጁማ

ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ በርካታ ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነገረ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ኬንያዊው ጋዜጠና ያሲን ጁማ አንዱ ነው።

በአገሪቱ ውስጥ ፖለቲከኞችና የታሰሩ ጋዜጠኞች እንዳሉ የተነገ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አንዱ ኬንያዊው ጋዜጠኛ ያሲን ጁማ ይገኝበታል።

ያሲን በፖሊሶች ቁጥጥር ስር የዋለው ከሳምንት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው የአቶ ጃዋር መሐመድ መኖሪያ ቤት ውስጥ በነበረበት ጊዜ እንደሆነ ተግለጿል።

ኬንያዊው ጋዜጠኛ ያሲን ጁማ አዲስ አበባ ከመያዙ በፊት ሐሙስ ሰኔ 25 ቀን ከሰዓት በኋላ ከጓደኛው ጋር ሲያደርግ በነበረው የጽሑፍ መልዕክት ልውውጥ ላይ፤ በአቶ ጃዋር መሐመድ ቤት እንደሚገኝና ቤቱም በጸጥታ ኃይሎች እንደተከበበ ጽፎለት እንደነበረ ለቢቢሲ ተናግሯል።

የጋዜጠኛው በአቶ ጃዋር መሐመድ ቤት ውስጥ መያዙን በተመለከተ ለማጣራት ቢቢሲ በቤቱ ውስጥ ነዋሪ የሆኑና ከጃዋር የቤተሰብ አባል እንደተረዳው ያሲን ጁማ ከዚያው ቤት በጸጥታ ኃይሎች ተይዞ መወሰዱን አረጋግጧል።

ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ በቁጥጥር ስር የዋለው አቶ ጃዋር ሐሙስ ዕለት ፖሊሶች ቤቱን ለመፈተሽ ይዘውት በመጡበት ቀን ነው ያሲን የተያዘው። የቤተሰቡ አባል ለቢቢሲ እንደተናገሩት ፖሊሶች "ያሲንን ጨምሮ ሌሎች ሦስት ሰዎችን ይዘው ሄደዋል።"

የጋዜጠኛ ያሲን ጁማ ቤተሰብና ጓደኞቹ ኢትዮጵያ ውስጥ የመታሰሩን ዜና ይስሙ እንጂ ወደ የት እንደተወሰደና የት እንዳለ እስካሁን የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል።

የያሲን ባለቤት የሆነችው አሻ መሐመድ እንደምትለው፤ ባለቤቷ የት እንደሚገኝ የምታውቀው ነገር የለም። ለመጨረሻ ጊዜ ያነጋገረችውም ታሰረ በተባለበት ዕለት እንደሆነና የመታሰሩን ዜና የሰማችው 'ሲቲዝን' የተባለው የኬንያ ቴሌቪዥን ጣቢያ እስሩን በዘገበበት ወቅት ነው።

በመጨረሻ በተያዘበት ዕለት በዋትስአፕ መልዕክት ሲለዋወጡ እንደነበር ገልጻ፤ በመጨረሻም የጸጥታ ሰዎች አብረውት እንዳሉ ገልጾ መደወል እንዳቆም እንደነገራት ለቢቢሲ ተናግራለች።

የጋዜጠኛው ባለቤት አሻ መሐመድ፤ በአሁኑ ጊዜ ባሏ የትና በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ምንም መረጃ እንደሌላት ገልጻ፤ ባለቤቷ የት እና ለምን እንደታሰረ ለማጣራት ጥረት ብታደርግም እስካሁን ምላሽ ማግኘት እንዳልቻለች ትናገራለች።

ጉዳዩን በሚመለከትም "ለኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ኢሜይል ጽፌ ነበር፤ አልመለሱልኝም። ስልክ ስደውልም ስልካቸው አይሰራም። ወደ ኢትዮጵያ ለመሄድ ብፈልግም በኮሮናቫይረስ ምክንያት መሄድ አይቻልም ተባልኩ" ትላለች።

በአዲስ አበባ የሚገኘው የኬንያ ኤምባሲ በበኩሉ ታስሯል ስለተባለው ጋዜጠኛ ባወጣው መግለጫ፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ ኬንያውያንን መዝግቦ እንደሚይዝ ጠቅሶ ያሲን ጁማ የሚባል ኬንያዊ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለመኖሩ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ አመልክቷል።

ኤምባሲው ጨምሮም የተነሳውን ጉዳይ ተከትሎ ያሲን ጁማ በመባል የተገለጸው ግለሰብ በእስር ላይ መሆኑን ለማረጋገጥ ወደ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ደብዳቤ መጻፉን ገልጿል።

ቢቢሲ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ጄይላን አብዲ ታሰረ ስለተባለው ጋዜጠኛ ያሲን ጁማ እስካሁን ባላቸው መረጃ በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንደሌላ ተናግረው፤ ሌሎች የሚመለከታቸው የመንግሥት የጸጥታ ኃይል አካላት ጋር አጣራለሁ ብለዋል።