ዴሞክራቱ ባይደን ምርጫውን ካሸነፉ የትራምፕን የዓለም ጤና ድርጅት ውሳኔ እንደሚቀለብሱ ተናገሩ

የዴሞክራት እጩው ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የዴሞክራት እጩው ጆ ባይደን ምርጫውን ካሸነፉ፤ አሜሪካን ከዓለም ጤና ድርጅት ያስወጣውን የፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ እንደሚቀለብሱ ተናገሩ።

ፕሬዘዳንት ትራምፕ አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት እንደምትወጣ የተናገሩት ግንቦት ላይ ነበር። ሂደቱን የጀመሩት ደግሞ በዚህ ሳምንት ነው። ሂደቱ ቢያንስ አንድ ዓመት ይወስዳል።

ትራምፕ፤ የዓለም ጤና ድርጅት በቻይና ቁጥጥር ሥር ነው ብለው ስለሚያምኑ ነው ከድርጅቱ አሜሪካን ለማግለል ውሳኔ ያሳለፉት።

ለፕሬዘዳንትነት በሚፎካከሩት ትራምፕና በባይደን መካከል የአስር ነጥብ ልዩነት አለ። በርካታ መራጮች ወቅታዊው አስተዳደር ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሰጠው ምላሽና የአገሪቱ ምጣኔ ኃብት ጉዳይ ላይ ጥያቄ አላቸው።

በአገሪቱ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሲሆኑ፤ ከ130,000 በላይ ሰዎች ሞተዋል።

ጆ ባይደን ባለፈው ማክሰኞ በትዊተር ገጻቸው እንዳሉት፤ አሜሪካ የጤናን ጉዳይ በተመለከተ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር ብትተባበር መልካም ነው።

“ፕሬዝዳንት ከሆንኩ በኋላ በመጀመሪያው የሥራ ቀን የዓለም ጤና ድርጅትን በተመለከተ የተወሰነውን ቀልብሼ ወደ ዓለም አቀፍ መሪነታችን እንድንመለስ አደርጋለሁ” ብለዋል።

በአገሪቱ ምክር ቤት የውጪ ጉዳይ ክፍል ካሉ ዴሞክራቶች አንዱ የሆኑት ሮበርት መነንዴዝ፤ “በወረርሽኝ ወቅት ፕሬዘዳንቱ አሜሪካን ከዓለም ጤና ድርጅት አስወጥተዋል፤ አሜሪካን የሚያሳምም፣ አሜሪካውያንን ብቸኛ ሚያደርግ ውሳኔ ነው” ብለዋል።

ቻይናም ድሃ አገራት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል ስትል የፕሬዘዳንት ዶናልድን ውሳኔ ኮንናለች።

የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ዛሆ ሊያን “የአሜሪካ ውሳኔ ዓለም አቀፍ ትብብርን ያንኳስሳል። በተለይም ዓለም አቀፍ ድጋፍ የሚፈልጉ ታዳጊ አገሮች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል” ብለዋል።

አሜሪካ ዓለም አቀፍ ግዴታዋን እንድትወጣም አሳስበዋል።

አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት የምትወጣው ለምንድን ነው?

አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን ለሲቢኤስ ኒውስ እንደተናገሩት፤ የዓለም ጤና ድርጅት የአሠራር ለውጥ እንዲያደርግ አሜሪካ ብትጠይቅም ድርጅቱ ፈቃደኛ አልሆነም።

አሜሪካ ከድርጅቱ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማቋረጥ የተወሰነውም ለዚህ ነው።

ፕሬዘዳንት ትራምፕ፤ ድርጅቱ ራሱን እንዲያሻሽል ግንቦት ላይ የ30 ቀን ገደብ ሰጥተው እንደነበር ይታወሳል። ካልሆነ ግን ከድርጅቱ ወጥተው ድጋፋቸውን ወደ ሌሎች ዓለም አቀፍ የሕብረተሰብ ጤና የተራድኦ ድርጅቶች እንደሚያዞሩ ተናግረዋል።

“ቻይና ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ቀስቅሳለች። በቻይና መንግሥት ስህተት ሳቢያ ዓለም እየተንገላታ ነው” ብለውም ነበር።

ፕሬዘዳንቱ ማስረጃ ባያቀርቡም፤ ቻይና የዓለም ጤና ድርጅት ዓለምን እንዲያሳስት አድርጋለች ሲሉ ተደምጠዋል።

አሜሪካ ከድርጅቱ አባል አገራት ከፍተኛውን የገንዘብ አስተዋጽኦ ታደርጋለች። ባለፈው ዓመት 440 ሚሊዮን ዶላር የደጎመች ሲሆን፤ ይህም ከድርጅቱ ጠቅላላ በጀት 15 በመቶው ነው።

እአአ 1948 ላይ በወጣ የአገሪቱ ሕግ መሠረት፤ አሜሪካ የአንድ ዓመት ማሳሳቢያ ሰጥታ፣ ክፍያ ፈጽማ ከድርጅቱ መውጣት እንደምትችል ተደንግጓል።

1948 ላይ የተቋቋመው የዓለም ጤና ድርጅት 194 አባላት አሉት። ከአባል አገራት ክፍያ በተጨማሪ በበጎ ፍቃደኞች እርዳታ ይንቀሳቀሳል።

ኮሮና