ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች አገራት ከኮቪድ-19 በባሰ በረሃብ በርካቶች ሊሞቱ ይችላሉ ተባለ

በኮሮናቫይረስ ሰበብ በተከሰቱ ቀውሶች ሳቢያ ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ አገራት ውስጥ በወረርሽኙ ከሚሞቱ ሰዎች ቁጥር የሚበልጡ በረሃብ ምክንያት ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ ኦክስፋም አስታወቀ።

ኦክስፋም እንዳለው ኮቪድ-19 ለወትሮው በረሃብ እየተሰቃየ ባለው ዓለም ላይ የከፋ ረሃብን አስከትሏል። በዚህም በተለይ አስር አገራት ክፉኛ ችግር እንደሚገጥማቸው የገለጸ ሲሆን ኢትዮጵያም አንዷ እንደሆነች አመልክቷል።

ድርጅቱ ባወጣው የአስር አገራት ዝርዝር ውስጥ አብዛኞቹ የሚገኙት በአፍሪካና በእስያ አህጉር ሲሆን እነሱም ኢትዮጵያ ፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ የመን፣ ሶሪያ፣ አፍጋኒስታን፣ ቬንዝዌላ፣ ምዕራብ ሳህል እና ሄይቲ ናቸው።

ኦክስፋም ጉዳዩን በሚመለከት ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው ኮሮናቫይረስ በዓለም ላይ የነበረውን የረሃብ ቀውስ ከማባባሱም በላይ ረሃብ ተከስቶባቸው የማያውቁ አዳዲስ አካባቢዎችን እየፈጠረ ነው ብሏል።

በዚህም መሰረት ከወራት በኋላ በየቀኑ ከ6ሺህ እስከ 12 ሺህ የሚደርሱ ሰዎች በኮቪድ-19 ምክንያት በሚከሰት ረሃብ ሳቢያ በዓለም ዙሪያ ለሞት ሊዳረጉ ይችላሉ ብሏል።

ይህም አሃዝ የኮሮናቫይረስ ከሚገድላቸው ሰዎች በከፍተኛ ደረጃ የሚልቅ እንደሚሆን ኦክስፋም አስጠንቅቋል።

የተራድኦ ድርጅቱ እንዳለው፤ ሥራ አጥነት፣ ምግብ አምራቾች በእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት መሥራት አለመቻላቸው እንዲሁም እርዳታ ለማከፋፈል አዳጋች መሆኑ ረሃቡን ያባብሰዋል።

መንግሥታት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን መስፋፋት ለመግታት ከሚያደርጉት ጥረት ጎን ለጎን የተጋረጠውን የረሃብ ቀውስ ለመቆጣጠር አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱም ጠይቋል።

ድርጅቱ እንዳለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም ላይ እየጨመረ በነበረው የረሃብ ችግር ላይ አባባሽ ምክንያት ሆኗል።

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በዓለም ዙሪያ 821 ሚሊዮን ሰዎች የምግብ ዋስትና ችግር ያጋጠማቸው ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ በከባድ ወይም በከፋ ረሃብ ለስቃይ የተዳረጉት 149 ሚሊዮን ሰዎች ይሆናሉ።

በአሁኑ ወቅትም ኮሮናቫይረስ በየአካባቢው ከሚከሰቱ ግጭቶች፣ እየጨመረ ከመጣው የኑሮ ልዩነትና እየተባባሰ ካለው የአየር ጸባይ ለወጥ ጋር ተዳምሮ የተዳከመውን የዓለም የምግብ አቅርቦት ሥርዓት በመጉዳት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ድሆችን ወደ ረሃብ አፋፍ አድርሷቸዋል ብሏል።