ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከእንቅስቃሴ ገደቡ ጋር ተያይዞ በኤርትራ የመሰረታዊ ሸቀጦች እጥረት አጋጠመ
በኤርትራ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በተወሰዱ እርምጃዎች ምክንያት የመሰረታዊ ሸቀጦች እጥረት ማጋጠሙን፣ ገበያ ላይ ባሉት ሸቀጦችም ላይ የዋጋ ንረት በመታየቱ ለከፋ ችግር እየተጋለጡ መሆኑን ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች ገለጹ።
በኤርትራ ቆላማ አካባቢዎች በተለይ በጋሽ ባርካ አካባቢ ሁኔታው የባሰ እንደሆነና በተለይም ሃይኮታ በሚባሉ የገጠር አካባቢዎች ህጻናት ለረሃብ እየተጋለጡ እንደሆነ የቢቢሲ ምንጮች ተናግረዋል።
የሸቀጦች እጥረቱ ያጋጠመው በአብዛኛው የኤርትራ ከተሞች እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን በአንድ ሺህ ናቅፋ ሲሸጥ የነበረው 'የማሽላ ወዲ ዓከር' ጥሬ በአሁኑ ወቅት ሁለት ሺህ ናቅፋ እየተሸጠ መሆኑን ምንጮቹ ገልጸዋል።
በተጨማሪም በአገሪቱ ያለው የውሃ እጥረት አሳሳቢ እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል፤ ይህንን እጥረት ለማቃለልም ከዚህ በፊት በውሃ ጫኝ መኪኖች ውሃ ይታደል የነበረ ቢሆንም አሁን ግን በወረርሽኙ ምክንያት ባጋጠመ የነዳጅ እጥረት ሳቢያ መኪኖቹ አገልግሎታቸውን እንደቀነሱ ተነግሯል።
የኤርትራ መንግሥት ወረርሽኙን በተመለከተ ቀደም ብሎ በሰጠው መግለጫ "ድንበሮችን እና ቤታችንን ዘግተን ከመከላከሉ ውጪ አማራጭ የለንም" ማለቱ ይታወሳል።
ስለሆነም ዜጎች ምግብ ለመግዛትና ለአስገዳጅ ነገሮች ካልሆነ በስተቀር ከቤታቸው እንዳይወጡ ሰለተነገረ ቤቶቻቸውን ዘግተው እንደሚገኙ ነዋሪዎች ገልጸዋል።
'ሕድሪ' ከሚባሉት በመንግሥት ድጎማ ሸቀጦችን ከሚያከፋፍሉ ሱቆች እንደ ማሽላ፣ ዘይት፣ የሻይ ቅጠል እና ስኳርን የመሳሰሉ ሸቀጦችን ሲገዙ የነበሩ የአሥመራ ከተማ ነዋሪዎች እጥረት በማጋጠሙ ለችግር እንደተጋለጡ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ዜጎች በቅርበት ምግብና ሌሎች ሸቀጦች ያስገቡባቸው የነበሩት የሱዳን እና የኢትዮጵያ ድንበሮችም ዝግ በመሆናቸው ችግሩ እንደተባባሰ ተጠቅሷል።
ስማቸውን ሳይጠቅሱ ለቢቢሲ አስተያየታቸውን የሰጡ አንዳንድ ነዋሪዎች እንዳሉት መንግሥት ለወረርሽኙ መከላከያ ከአገር ውስጥና ከውጭ ገንዘብ እያሰባሰበ በመሆኑ እርዳታ ያደርግልን ይሆናል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ከውጭ አገራት ገንዘብ የተላከላቸው ቤተሰቦች ከሃዋላ ድርጅቶች ተደውሎ "ገንዘባችሁ መጥቷል እንቅስቃሴ ሲፈቀድ መውሰድ ትችላላችሁ" መባላቸውን ገልጸው፤ የእንቅስቃሴ ገደቡ ዕለታዊ ፍላጎቶቻቸው ለማሟላት አዳጋች እንዳደረገው ይገልጻሉ።
አንዳንድ የአካባቢ አስተዳደሮች በወረርሽኙ ምክንያት በጥብቅ የተጎዱትን ለመደገፍ የሚውል እህል ከአርሶ አደሮች እየሰበሰቡ እንደሆነም ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ኤርትራ በኮሮናቫይረስ ስጋት ድንበሮቿን ዘግታ ዜጎቹም በየቤታቸው እንዲቀመጡ ካደረገች ሦስት ወር ተቆጥሯል። በአገሪቱ ያለው የበሽታ መስፋፋትም እጅግ ዝቅተኛ ከሙባለው ደረጃ ላይ እንደሆነ ይፋዊ መረጃዎች ያመለክታሉ።