ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቆመ አውሮፕላን የገጨው አብራሪ ምርመራ ሊደርግበት ነው
የአየር በረራዎች ቆመዋል በሚባሉበት በአሁኑ ወቅት ቆሞ የነበረን አውሮፕላን የገጨው ፓይለት ላይ ምርመራ ሊደረግ ነው።
ግጭቱ የተከሰተው ማክሰኞ ማምሻውን ነው። አበርዲን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተሰኘው የስኮትላንዱ ጣቢያ።
አንድ አነስ ያለ አውሮፕላን መስመሩን ጠብቆ የቆሞ ተለቅ ያለ አውሮፕላን ይገጫል። የአነስተኛው አውሮፕላን አፍንጫ ተለቅ ካለው አውሮፕላን ክንፍ ሥር እንደ እርጎ ዝንብ ጥልቅ ይላል።
አልፎም በአፍንጫው የትልቁን አውሮፕላን ክንፍ ወደ ላይ ከፍ ያደርገዋል። አገር ሰላም ብሎ የቆመው አውሮፕላን የሎጋንኤር ንብረት ነው። ነገር ተንኳሹ ደግሞ የፋልይቢ።
ትልቁ አውሮፕላን ያሳፈራቸውን መንገደኞች ከነሻንጣቸው ወደ መዳረሻቸው ከሸኘ በኋላ ነው መስመሩን ጠብቆ የቆመው ተብሏል።
የአገሪቱ የአውሮፕላን አደጋዎች መርማሪ ተቋም ጉዳዩን ለእኔ ተዉት እመረምረዋለሁ ብሏል።
በግጭቱ ማንም አልተጎዳም።
ሎጋንኤር አውሮፕላኔ በቆመበት ተገጭቷል ሲል መግለጫ አውጥቷል። "ኢምብራዬር 145 የተሰኘው ጄታችን መንገደኞችም ሆኑ የበረራ ሠራተኞች በሌሉበት ቆሞ ሳለ በፍላይቢ ቦምባርዲኤር Q400 ተገጭቷል። ገጪው አውሮፕላን ለበረራ እየተዘጋጀ እንደነበር ተረድተናል።"
መግለጫው አክሎ "የገጭው አውሮፕላን አፍንጫ የእኛን አውሮፕላን የቀኝ ክንፍ ጭሮታል፤ ከመሬት ወደ ላይም ቀና አድርጎታል። ዋናው ነገር ማንም አለመጎዳቱ ነው። የፍላይቢው አውሮፕላን ሠራተኞች ሰላም መሆናቸው በጎ ዜና ነው።"
አበርዲን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያም "አዎ እውነት ነው፤ ማክሰኞ ምሽት 12፡00 ገደማ ግጭቱ ተከስቷል" ሲል አረጋግጧል። አየር ማረፊያው አክሎም አደጋው ምርመራ እየተደረገበት እንደሆነ ጠቁሟል።
አውሮፕላኖች በቆሙበት ሲጋጩ እምብዛም አይስተዋልም። ለዚህም ነው ዜናው ከአውሮፓ አልፎ በዓለም የናኘው።
ዜናው ያስደነቃቸው የማኅበራዊ ድር-አምባ ተጠቃሚዎች በሁኔታው ሲያፌዙ ተስተውለዋል። አንድ ፌስቡከኛ "አውሮፕላኖች አካላዊ ርቀት መጠበቅ ተዉ እንዴ?" ሲል ፅፏል።