ትዊተር የትራምፕ ያሰፈሩት መልዕክት 'አሳሳች ሊሆን ይችላል' አለ

ትዊተር ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በገጻቸው ያሰፈሩት መልዕክት አሳሳች ሊሆን ስለሚችል ለመጀመሪያ ጊዜ 'ማጣራትን የሚፈልግ ሊሆን ይችላል' የሚል ማሳሰቢያ አስቀመጠ።

ዶናልድ ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ባሳፈሩት መልዕክት ስር መልዕክቱን የሚያነቡ ሰዎች በፕሬዝደንቱ የሰፈረው መልዕክ እውነተኛነትን እንዲያጣሩ የሚመክር ምልክት ትዊተር አኑሯል።

ትዊተር ዶናልድ ትራምፕ በገጻቸው ላይ ያሰፈሩት መልዕክት 'አሳሳች ሊሆን ይችላል' ያለው የራሱን 'አሳሳች መረጃ ፖሊስ' መሠረት በማድረግ ነው።

ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው 'በፖስታ አማካኝነት የሚላክ እና የሚመለስ የድምጽ መስጫ ሥርዓት ትክክለኛ ውጤትን አያሳይም' የሚል ሃሳብ ያለው ጽሑፍ ነበር በትዊተር ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት።

ትዊተር እውነትነታቸው በሚያጠራጥሩ የትዊተር መልዕክቶች ስር ተጠቃሚዎች ስለተጠቀሱት ጉዳዮች ተጨማሪ መረጃዎችን እንዲያጣሩ ለማሳሰብ ሰማያዊ የቃለ አጋኖ [ ! ] መልዕክት የስቀምጣል።

ዶናልድ ትራምፕ ለትዊተር ምላሽ ይሆን ዘንድ፤ የማኅበራዊ ሚዲያው መድረኩ 'ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ያፍናል' ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ጸፈዋል።

ትዊተር በገጹ ላይ የሚወጡ ሐሰተኛ ወይም አሳሳች መልዕክቶች ላይ ሰማያዊን ቃለ አጋኖ መልዕክት ማስቀመጥ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

አሜሪካ ከአምስት ወራት በኋላ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ታካሂዳለች። ትራምፕ የሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው ለሁለተኛ ዙር የሚወዳደሩ ሲሆን ዲሞክራቱ ጆ ባይደን ደግሞ የትራምፕ ተቀናቃኝ ሆነው ይቀርባሉ።

በዚህ ምርጫ የኮሮናቫይረስ ስጋት የሚቀጥል ከሆነ፤ አሜሪካውያን ወደ ምርጫ ጣቢያ ሳይሄዱ በፖስታ ቤት በኩል በሚላክ የደምጽ መስጫ ወረቀት ላይ የሚሹትን እጩ ይምረጡ የሚለው አማራጭ በስፋት እየተመከረበት ነው።

አንድ የምርምር ተቋማ ይፋ እንዳደረገው 66 በመቶ የሚሆኑ አሜሪካውያን ድምጻቸውን ለመስጠት ወደ ምርጫ ጣቢያ የመሄድ ፍላጎት የለንም ብለዋል። ለዚህም ዋነኛ ስጋታቸው ለኮሮናቫይረስ ልንጋለጥ እንችላለን የሚለው ነው።

ዋሽንግተን፣ ኦሪጎን እና ኮሎራዶን ጨምሮ አምስት የአሜሪካ ግዛቶች ምርጫን የሚያካሂዱት በፖስታ የሚላኩ የምርጫ ድምጽ መስጫ ወረቀቶች ላይ በመመስረት ነው።