በሩዋንዳው ጭፍጨፋ ተፈላጊው ሰው በቁጥጥር ሥር ሳይውል እንዴት ለ26 ዓመታት ሊደበቅ ቻለ?

ፈሊሴ ካቡጋ የኢንተርሃምዌይ ሚሊሻዎች የመንፈስ አባት ይሉታል። ያኔ የተገደሉት የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ጁቬናል ሃቢያሪማና የቅርብ ወዳጅም ነበር። ቤተሰብም ነበር፤ አረ በጋብቻም ተሳስሯል።

በዚያ ዘመን እጅግ የናጠጠው የሩዋንዳ ዜጋም ፈሊሴ ካቡጋ ነበር። ሻይ ቅጠል ንግድ የእርሱን ያህል የነገደ አፍሪካዊ አልነበረም።

ካቡጋ በጣም አስፈሪ፣ በጣም ጨካኝ፣ በጣም ጉልበተኛ እንደነበር ይነገራል።

ጨፍጫፊዎችን አስታጥቶ ያደራጀ፣ ለነፍስም ለሥጋም ትጥቅና ስንቅ ያቀበለ፣ ለቱትሲዎች መጨፍጨፊያ ይሆን ዘንድ ካራ ከነመሞረጃው ወደ አገር ቤት በገፍ ያስገባው እርሱ ነበር ይባላል።

የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ይነዛ የነበረው አርቲኤልኤም (RTLM) ራዲዮ ጣቢያ ባለቤትም ነበር። ፈሊሴ ካቡጋ በዘር ማጥፋት ወንጀል ከሚፈለጉት ሰዎች ቁጥር አንዱ ብቻም ሳይሆን አየሁት ለሚል 5 ሚሊዮን የሚያሸልም ውድ ወንጀለኛ ነበር።

ነገር ግን 26 ዓመት ሙሉ ቢፈለግ ቢፈለግ አልተገኘም። በቀደም ለታ ፓሪስ አቅራቢያ ተያዘ።

እንዴት ተያዘ አይደለም አሁን ዋናው ጥያቄ? እንዴት ለ26 ዓመታት በሰላምና በጤና፣ በተድላና በፍሰሀ በፈረንሳይ ያውም የዓለም ዋና ከተማ በምትባለው ፓሪስ አቅራቢያ ሊደበቅ ቻለ?

ካቡጋን ያየ፣ ያለበትን የሚያውቅ 5 ሚሊዮን ዶላር ይሸለማል

28 የተለያዩ ማንነቶችና ስሞች ነበሩት። በሁለት አህጉሮች ውስጥ ሲሽሎኮሎክ ቆይቷል። በአፍሪካና በአውሮፓ ምናልባትም እጅግ ቁልፍ ከሚባሉ ሹሞች ጋር ተመሳጥሯል። ማንነቱና 'የት'ነቱ ሳይደረስበት እንዲቆይ ሀብቱን አፍስሷል።

በ84 ዓመቱ ታዲያ ባለፈው ሳምንት ተጋለጠ። እንዴት ተደረሰበት? ማን ደረሰበት? የሚለው አሁንም በደንብ አልተብራራም።

መሴይ ሰርግ ብራመርዝ በተባበሩት መንግሥታት የጦር ወንጀለኞች አቃቢ ሕግ ናቸው። በተለይ በሩዋንዳና በዩጎዝላቪያ ለተፈጸሙ ወንጀሎች ዋና አቃቢ ሕግ ሆነው ሠርተዋል።

ይህ ከእንግዲህ ዋጋ የለውም ተብሎ የተዘጋውን ፋይል የከፈቱትም እርሳቸው ናቸው።

"ካቡጋ ወይ እንግሊዝ፣ ወይ ቤልጂየም፣ ወይ ፈረንሳይ ተደብቆ እንደሚኖር ፍንጭ ያገኘነው ከአንድ ዓመት በፊት ነበር። ሆኖም ገና የዛሬ 2 ወር ግድም ነው በፈረንሳይ ስለመኖሩ ማረጋገጥ የቻልነው" ሲሉ ያስረዳሉ እኚሁ አቃቢ ሕግ መሴይ ሰርግ ብራመርዝ፤ ለቢቢሲ።

ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ታዲያ የፈረንሳይ የደኅንነት ሰዎች ካቡጋ የሚኖርበትን አፓርትመንት ደረሱበት። ካቡጋ ከፓሪስ ወጣ ብላ በምትገኝ አንዲት መለስተኛ መንደር ነበር የሚኖረው። ያውም እዚህ ግባ በማይባል መናኛ ሰፈር ውስጥ በሚገኝ መናኛ የመኖርያ ሕንጻ። ሕንጻው በፍጹም የሚሊየነር ሕንጻ አይመስልም።

ካቡጋን አንዱ እንዲሸሽ ያደረገው በወንጀሉ ልጆቹ ተሳትፎ ስለነበራቸው ነበር ይላል አቃቢ ሕግ።

ካቡጋ ማን ነው? ማንስ ነበር?

ካቡጋ በዚያ ዘመን በሩዋንዳ ሃብታሙ ሰው ነበር ብለናል። ቢያንስ አምስት ልጆች አሉት። ሁለቱ ሴት ልጆች ያገቡት ያን ጊዜ ፕሬዝዳንት የነበሩት የጁቬናል ሃቢያሪማና ወንድ ልጆችን ነበር።

እኚህ ፕሬዝዳንት እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ በሚያዚያ 6/1994 ከአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ሲመለሱ አውሮፕላናቸው ተመትቶ ተጣለ። የእርሳቸው መገደልን ተከትሎ ነበር ሁቲዎች በይፋ ቱትሲዎችን እያደኑ መቅላት የጀመሩት።

ፕሬዝዳንት ሃቢያሪማና የተሳፈሩበት አውሮፕላንን መትቶ የጣለው ማነው የሚለው ሲያወዛግብ ነበር። ፕሬዝዳንቱ ሁቱ በመሆናቸው የአሁኑ ፕሬዝዳንትና የዚያኔው ተቀናቃኛቸው ቱትሲው ፖል ካጋሜና ጦራቸው ነው ለዚህ ተጠያቂው ሲባል ቆይቷል። በመጨረሻ አክራሪ ሁቱዎች ራሳቸው ሁቱውን ፕሬዝዳንት እንደገደሏቸው ተረጋግጧል።

በዚህ ወንድም በወንድሙ፣ እናት በልጇ፣ ባል በሚስቱ፣ አባት በልጆቹ ላይ ሳይቀር ካራውን ባነሳበት የዓለም እጅግ አሰቃቂው የክፍለ ዘመኑ የዘር ጭፍጨፈፋ የካቡጋ ሚና የላቀ ነበር።

በአጭሩ የዘር ጭፍጨፋውን ስፖንሰር ያደረገው ካቡጋ ነው ይላሉ የሩወንዳን ታሪክ አጥኚዎች።

የፈረንሳይ የጸጥታ ኃይሎች ካቡጋን ሊደርሱበት የቻሉት የልጆቹን ዱካ ተከትለው በመሄድ ነበር። ካቡጋ በአንዲት ስሟ ባልተገለጸች የአፍሪካ አገር ፓስፖርት በሐሰት ስምና ማንነት እዚያ አፓርትመንት 3ኛ ፎቅ ላይ ተቆምጦ የተገኘውም በዚሁ ዘዴ ነው።

ኮሎኔል ኤሪክ ኢማሩክስ የምርመራ ቡድኑን የመሩ ፈረንሳዊ ናቸው። "ኮሮናቫይረስ ሰዎች ቤታቸው እንዲቀመጡ ስላደረገ የምርመራ ቡድኑ በተለየ ትኩረት ሰውየውን እንዲያድነው ምቹ ጊዜና ሁኔታን ፈጥሯል" ሲሉ ተናግረዋል።

በሻይ ቅጠል እርሻ ንግድ ሚሊየነር የሆነው ካቡጋ ለሁቱ አማጺያን የቱትሲ ጎሳዎችን መጨፍጨፊያ ይሆን ዘንድ ከዩኒፎርም ጀምሮ ትጥቅና ስንቅን እንዳቀበለው ሁሉ የብዙዎችን አስተሳሰብ የመረዘውን ፕሮፓጋንዳ ሲቀምም ነበር።

በመቶ ሺዎች ካራ ገዝቶ ወደ ሩዋንዳም የማስገባቱን ያህል በዚህ በባለቤትነት በሚያስተዳድረው የሬዲዮ ፕሮፓጋንዳ ማሽን በጥላቻ የተሞሉ ሁቱዎችን አእምሮ ስል አድርጎት ነበር ተብሎም ይታማል።

በሩዋንዳ በመቶ ቀናት ብቻ 800 ሺህ ዜጎች ተጨፍጭፈዋል። አንዳንዶች ቁጥሩን ወደ አንድ ሚሊዮን ያስጠጉታል። ይህም ማለት ከጠቅላላው የሩዋንዳ ሕዝብ በአማካይ ከ10 ሩዋንዳዊያን አንዱ በዚያ ዘመን አሰቃቂ የዘር ፍጅት ተገድሏል ማለት ነው።

ጭፍጨፋውን ተከትሎ የካጋሜ አማጺ ቡድን አገሪቱን ሲቆጣጠር የበቀል እርምጃን በመፍራት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሁቱዎች ወደ ጎረቤት የአሁኗ ዲሞክራቲክ ኮንጎና (ዛየር) ቡሩንዲ ሸሽተው ነበር።

አሁን የዓለም መገናኛ ብዙሃንም ሆነ ሩዋንዳዊያን እየጠየቁ ያሉት ጥያቄ አንድ ነው።

እንዴት ይህ ሰው ለ26 ዓመታት ሊደበቅ ቻለ? የሚለው።

አሜሪካ እሱ ያለበትን ለጠቆመ አምስት ሚሊዮን ዶላር እሸልመዋለሁ ብላ ዋጋ ያወጣችለት ወንጀለኛ ለዚህን ያህል ጊዜ ሊሸሸግ ይቻለዋል?

እጅግ በተራቀቀው የምዕራቡ ዓለም የደኅንነት መዋቅር እንዴት ላይደርስበት ቻለ? ሰውየው ያውም ከኢንተርፖል ዋና ጸሕፈት ቤት አፍንጫ ሥር ተቀምጦ ሊገኝ ቻለ? ምናልባት አዳኞቹ ራሳቸው ዳባቂዎቹ ይሆኑ?

ኬንያና ካቡጋ

ካቡጋ በተለያዩ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት በተለይም በኬንያ ውስጥ ተሸሽጎ እንደነበር ይገመታል። እሱ እና ቤተሰቡ ከኬንያ ጋር ጥብቅ የንግድ ግንኙነት እንደነበራቸው ከበቂ በላይ ማስረጃዎች አሉ።

በኬንያ የተንሰራፋው የሙስና ሰንሰለት ሰውየውን ለመደበቅ ምቹ ሁኔታ ሳይፈጥር እንዳልቀረ የሚገምቱም ብዙ ናቸው።

በፈረንጆች በ2006 የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ አጣሪ ኮሚሽን ካቡጋ ወይ በኬንያ ተደብቋል ካልሆነም ገብቶ ወጥቷል ሲል ጥርጣሬውን ገልጾ ነበር። ለዚህም ፍንጭ እንዳገኘ በወቅቱ በስፋት ተገልጾ ነበር።

ይህ ከተባለ ከሦስት ዓመት በኋላ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ስቴፈን ራፕ ናይሮቢ ሰውየውን አሳልፋ ላለመስጠት እያቅማማች ነው ሲሉ ከሰው ነበር።

እንዲያውም ካቡጋ በኬንያ አንዳንድ ቁልፍ የቢዝነስ ስብሰባዎች ላይ ጭምር ይገኝ እንደነበር የሚናገሩ አሉ።

በ2015 ደግሞ በኬንያ የካቡጋ ቤተሰብ ነው የተባለ ንብረትን በፍርድ ቤት ለማስመለስ ባለቤቱ ጆሴፊን ፍርድ ቤት ክስ መስርታ እንደነበርም ይነገራል።

ይህ በኬንያ የሚገኘው ንብረት ስፓኒሽ ቪላስ የሚባል የሪልስቴት ሀብት ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጦር ወንጀለኞች ንብረት እንዲታገድ በሚያዘው ስምምነት መሰረት የካቡጋ የሆነው ይህ ንብረትም ለሴትየዋ ጆሴፊን ሳይመለስ ቀርቷል።

የኬንያ መገናኛ ብዙሃን ለዓመታት ካቡጋ በናይሮቢ እንደሚገኝ ቢዘግቡም ጠጣር መረጃ አቅርበው ግን አያውቁም።

የኬንያ ፖሊስ በፈረንጆቹ በሐምሌ 1997 የሩዋንዳ ተጠርጣሪ ወንጀለኞችን ለመያዝ ድንገቴ ዘመቻ በከፈተበት ወቅት ካቡጋ ከባለሥልጣናት ቅድመ ጥቆማ በማግኘቱ መሰወሩ ተዘግቦ ነበር። ይህ ክስተት ከአንዴም ሁለት ሦስቴ ተደጋግሟል።

ይህ የሚያሳየው ምናልባት ሰውየው በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ከለላ ይደረግለት እንደነበረ ነው።

የኬንያ ጋዜጠኞች የሰውየውን ዱካ ለማግኘት ሙከራ ሲያደርጉ ለአደጋ እንደሚጋለጡ ተደጋግሞ ይነገራል። በፈረንጆች 2003 የእርሱን ጉዳይ ተከታትሎ በመዘገብ የሚታወቀው ጋዜጠኛ ዊሊያም ሙኑሄ አፓርትመንቱ ውስጥ ባልታወቁ ሰዎች ተገድሎ ተገኝቷል።

ይህም በእራሱ በካቡጋ ትዕዛዝ እንደተፈጸመ ይታመናል።

ይህ ጋዜጠኛ ከሞተ በኋላ ወንድሙ ይፋ እንዳደረገው ከሆነ ጋዜጠኛ ሙኑሄ ከኤፍቢአይ ጋር በመተባበር የቢዝነስ ሰው መስሎ ካቡጋን ለመገናኘት ቀጠሮ ነበረው።

የኬንያ ፖሊስ በበኩሉ 'ጋዜጠኛው የሞተው የከሰል ጭስ አፍኖት ነው እንጂ ተገድሎ አይደለም' ሲል አስተባብሏል።

የሟች ወንድም ግን ወንድሙ በጥይት መገደሉን አይቻለሁ፤ ቤቱም በደም ተጨመላልቆ ነበር ሲል መስክሯል። "በጭስ የሞተ ሰው እንዴት በደም ሊጨቀይ ይችላል" ሲልም ጠይቋል።

ከዚህ ክስተት 8 ዓመት በኋላ ጆን አላን ማኑ የሚባል ሌላ ጋዜጠኛ በተቀነባበረ ስልት ካቡጋን የሚመስል ሰው ምስል በምስጢር ተልኮለት እሱም መረጃው ትክክል መስሎት ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ በተቀነባበረ ሁኔታ መታለሉ ይታወሳል።

ምንጮች ለዚሁ ጋዜጠኛ አሳሳች መረጃ የሰጡት ጋዜጠኛው የካቡጋ ነው የተባለ የባንክ ሂሳብ መረጃን ይፋ በማድረጉ እሱን ለማሳጣት ያለመ እንደነበር ተገምቷል።

ይህ እንዲሆን የተደረገው በተለይ ይህ ጋዜጠኛው በተከታታይ የካቡጋን ጉዳይ ተከታትሎ በመዘገብ ስላስቸገረ እሱን በሕዝቡ ዘንድ ለማሳጠት እንደነበር ይጠረጠራል።

ይህ ጆን አላን ማኑ የተባለው ጋዜጠኛ ከዚህ ክስተት በኋላ የግድያ ዛቻ ስለደረሰበት ከቤተሰቡ ጋር ሽሽት ገብቶ ነበር።

የካቡጋን በፓሪስ አቅራቢያ መያዝ ተከትሎ ይኸው ጋዜጠኛ ለቢቢሲ አስተያየቱን ሲሰጥ "የግለሰቡ ይህን ሁሉ ዘመን መሸሸግ መቻል የሚነግረን ነገር ቢኖር ኬንያን ጨምሮ ሌሎች አገራትም ለሰውየው ከለላ ይሰጡ እንደነበረ ነው" ብሏል።

ካቡጋ እስከዛሬ የት ነበር?

ካቡጋ የሩዋንዳ ጭፍጨፋን ተከትሎ መጀመርያ ወደ ስዊዘርላንድ እንዳቀና ይነገራል። ሆኖም እዚያ እንዲኖር ስላልተፈቀደለት ወደ አፍሪካ ለመመለስ ተገዷል።

በጊዜው የት አገር እንደተመለሰ ባይታወቅም በኮንጎ ኪንሻሳ በኩል ስለማለፉ ግን መረጃ አለ።

በተመሳሳይ በሆነ ዘመን ኬንያ ስለመቆየቱ መረጃዎች እንዳሉ በስፋት ቢነገርም አቃቤ ሕጉ ግን ኬንያ ብቻ ሳይሆን ማዳጋስካርና ቡሩንዲም ሰውየው ለተወሰነ ጊዜ መሸሸጉን አመልክቷል።

በ2007 በጀርመን ቀዶ ጥገና ሕክምና ስለማድረጉም መረጃዎች ወጥተዋል። ያን ጊዜ ሰውየውን ለምን መያዝ እንዳልተቻለ ግን የተባለ ነገር የለም።

በመጨረሻም ሰፊ የስልክና የገንዘብ ዝውውር መስመሮችን በመመርመር እና የልጆቹን ዱካ በመከተል ሰውየው ፈረንሳይ ውስጥ እንደሚኖር ፍንጭ መገኘቱን አቃቤ ሕጉ አብራርተዋል።

የዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ፌዴሬሽን ባልደረባ ፓትሪክ ባውዶይን እንደሚሉት "የከፍተኛ ባለሥልጣናት ድጋፍ ሳይኖርበ፤ ሰውየው በምንም ተአምር ፈረንሳይ ውስጥ ሊደበቅ አይችልም።"

ሂውማን ራይትስ ዋች የተባለው የመብት ተቆርቋሪ ቡድን በበኩሉ እንዴት ሰውየው ይህን ሁሉ ዓመት ከሕግ ተሸሸገ ለሚለው ምላሽ ለማግኘት ራሱን የቻለ ምርመራ እንዲጀመር በይፋ ጠይቋል።

ጎረቤቶቹ ምን አሉ?

ከፓሪስ ወጣ ብላ በምትገኝ ሰፈር ውስጥ ካቡጋን ይጎራበቱት የነበሩ የሰፈሩ ሰዎች ሰሞኑን በተሰማው ዜና ተደናግጠዋል።

በሬ ከአራጁ እንዲሉ ካቡጋን ያህል ወንጀለኛ ስለመጎራበታቸው የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ሆኖም ግን ቢያንስ ላለፉት አራት ዓመታት ሰፈር ውስጥ ወጣ ገባ ሲል ይመለከቱት እንደነበር መስክረዋል።

እሱ ይኖርበት የነበረው አፓርትመን የቤት ባለቤቶች ማኅበር ሊቀመንበር ኦሊቪየር ኦልሰን እንደሚያስታውሰው ሰውየው በጣም ቁጥብና ምስጢረኛ የሚመስል ሽማግሌ ሲሆን "እንደምን ዋሉ" ለሚለው የእግዜር ሰላምታ እንኳ የሚመልሰው በሹክሹክታ ነበር ብሏል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መጥቶ ቤት መቀመጥ ግዴታ ከመደረጉ በፊት፤ ግለሰቡ ዘወትር ለእግር ጉዞ ከቤቱ ይወጣ ነበር ይላሉ ጎረቤቶቹ።

ካቡጋ በአሁኑ ሰዓት ላ ሳንቴ በሚባል የፓሪስ ማዕከላዊ እስር ቤት ነው የሚገኘው።

ከዚህ በኋላም ከሆነ ከሆነ ዘ ሄግ ኔዘርላንድስ አልያም ታንዛኒያ አሩሻ ለሚገኘው የዘር ጭፍጨፋ ጉዳዮችን ለሚመለከተው ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ተላልፎ ይሰጣል።

የካቡጋ ጠበቃ ግን ደንበኛዬ ፍርዱ እንዲታይ የሚፈልገው እዚሁ ፓሪስ ነው ብለዋል።

በሩዋንዳ ጭፍጨፋ ባሎቻቸው የተገደሉባቸው ሴቶች ማኅበር ሰብሳቢ ቫለሪ ሙካባይሪ ለቢቢሲ ስትናገር "የሰውየው መያዝ ሁላችንንም ደስ አሰኝቶናል፤ በዚህ ዜና የማይደሰት የሰማዕታት ቤተሰብ የለም" ብላለች።