ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከ81 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን የአማራ ክልል አስታወቀ
ባለፉት ዓመታት በአማራ ክልል እና በሌሎች አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ተፈናቅለው የነበሩ ከ81 ሺህ በላይ ዜጎችን ወደ ቀያቸው መመለስ መቻሉን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትናና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዘለዓለም ልጃለም አስታውቀዋል።
"ከነዚህም ውስጥ 74 ሺህ 273 ሺህ በላይ በክልሉ እንዲሁም 6ሺህ 836 ከክልሉ ውጭ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ተደርጓል" ብለዋል።
በተከሰቱት ግጭቶች የሰው ህይወት ማለፉን፣ አካል መጉደሉን እና ንበረት መውደሙን የገለጹት በዚህም ምክንያት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በመጠለያ ካምፖች ለመኖር መገደዳቸውን አስታውቀዋል።
ተፈናቃዮቹ ወደቀዬአቸው ሲመለሱ እስከ 4 ወራት የሚደርስ ቀለብ እና ለእርሻ የሚሆን ግብዓት እንደተሟላላቸውም ገልጸዋል።
ከአማራና ቅማነት እንዲሁም በጃዊ አካባቢ በነበሩ ግጭቶች 7 ሺህ በላይ ቤቶች መቃጠላቸውን አመልክተው ከ5200 ሺህ በላይ ቤቶች እንደገና ሲገነቡ፣ ከ130 በላይ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶችም ጥገና ተደርጎላቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን አስታውቀዋል።
"ከቤንሻንጉል ክልል ተፈናቅለው ያልተመለሱ 4ሺህ 720 ዜጎች አሉ። ከክልሉ መንግስት ጋር በተደረገ ውይይት ሙሉ ለሙሉ ለመመለስ ፍላጎት አለ። ቻግኒ አካባቢ የነበሩ እና 4 ሺህ የሚያህሉ ሰዎች ባለፉት ቀናት ተመልሰዋል። ክልሉ ሁኔታዎችን አመቻችቶ ለመመለስ እየሰራ ነው። በሚመጡት ጥቂት ቀናት ቀሪዎቹ እንዲመለሱ እየተሠራ ነው" ብለዋል።
ምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር ከተፈናቀሉት ሁሉም በሚባል ደረጃ ወደ ቀዬአቸው መግባታቸውን አስታውቀዋል።
ለተፈናቃዮች የሚሆን ድጋፍ ለማሰባሰብ በተካሄደው ሥራ 720 ሚሊዮን ብር ቃል የተገባ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነውን መሰብሰብ መቻሉንም አስታውቀዋል።