ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ለአባታችን ገዳዮች ይቅርታ አድርገንላቸዋል" የሳዑዲው ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ልጅ
ከሁለት አመታት በፊት በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለው የሳዑዲው ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ልጅ ለአባቱ ገዳዮች ይቅርታ እንዳደረጉላቸው የሚገልፅ መግለጫ በዛሬው ዕለት አውጥቷል። በሰላ ትችቱ የሚታወቀው ጋዜጠኛ በቱርክ መዲና በሚገኘው የሳዑዲ ቆንስላ ውስጥ የተገደለው በጎርጎሳውያኑ 2018 ነበር።
የሳዑዲ ባለስልጣናት አሟሟቱን በተመለከተ ከሃገሪቱ መንግሥት በመጣ ትእዛዝ እንዳልሆነ ቢናገሩም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ በደህንነት አካላትና በተባበሩት መንግሥታት ዘንድ አመኔታን አላገኙም።
ጀማል ኻሾግጂ ከመሞቱ በፊት ነዋሪነቱን አሜሪካ ያደረገ ሲሆን ለዋሽንግተን ፖስትም ይፅፍ ነበር።
ጋዜጠኛው ቆንስላ ውስጥ ከገባ በኋላ መጥፋቱን ተከትሎ የሳዑዲ ባለስልጣናት እርስ በርስ የሚጣረሱ መረጃዎች ይሰጡ የነበረ ሲሆን በመጨረሻም ወደ ሳዑዲ እንዲያመጣው የታዘዘው ቡድን ተልዕኮው ወዳልሆነ አቅጣጫ አምርቶ መገደሉን አምነዋል።
በጎርጎሳውያኑ ታህሳስ 2019ም በጋዜጠኛው ግድያ እጃቸው አለበት የተባሉ አምስት ግለሰቦችን በሪያድ በተደረገ ሚስጥራዊ የፍርድ ሂደት ሞት ተፈርዶባቸዋል።
የተባባሩት መንግሥታት ልዩ ተወካይ አግነስ ካላማርድ የፍርድ ሂደቱን "የፍትህ ተቃራኒ" ሲሉ የጠሩት ሲሆን ነፃ ምርመራ መደረግም እንዳለበት አሳስበዋል።
የጀማል ኻሾግጂ ቤተሰቦች ምን አሉ?
መግለጫው በጋዜጠኛው ልጅ ሳላህ ሻሾግጂ ትዊተር ገፅ ላይ በዛሬው ዕለት የወጣ ሲሆን
"በዚች በተቀደሰች የረመዳን ወር አምላክ ያለንን እናስታውሳለን። የሰው ልጅ ይቅር ካለና እርቅ ማውረድ ከቻለ ሽልማቱ የሚገኘው ከአላህ ነው" በማለት ኑሮውን በሳዑዲ አረቢያ ጂዳ ያደረገው ሳላህ ፅፏል።
"ስለዚህም የሰማዕቱ ጀማል ኻሾግጂ ቤተሰቦች አባታችንን የገደሉትን ይቅርታ አድርገንላቸዋል፤ ሽልማቱንም ከአምላካችን እናገኘዋለን" በማለት በትዊተር ገፁ አስፍሯል።
በእስልምና ህግ መሰረት ቤተሰብም ይቅርታ ቢያደርግም የሞት ቅጣቱ ተፈፃሚ ይሆናል። በዚህ ሁኔታ ግን የሞት ቅጣቱ ተፈፃሚ ይሁን የታወቀ ነገር የለም።
ከዚህ ቀደም ሳላህ ሳዑዲ በምታደርገው ምርመራ እንደሚተማመንና ድጋፉንም እንደሚቸር ገልፆ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪም የአባቱን ሞት በመጠቀም የሃገሪቱን አመራር ሊያዳክሙ ይፈልጋሉ ያላቸውን "ተቃዋሚዎችና ጠላቶች" በማለትም ተችቷል።
የጀማል ኻሾግጂ ልጆች የአባታቸውን ሞት ተከትሎ ቤት፣ የወር ክፍያ በካሳነት እየተሰጣቸው እንደሆነ ባለፈው አመት ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል።
ከጋዜጠኛው ልጆችም መካከል የመጀመሪያ ልጁ ሳላህ ኻሾግጂ ብቻ ሳዑዲ አረቢያ በመኖር መቀጠሉንም ጋዜጣው አስነብቧል።
ጀማል ኻሾግጂ ላይ ምን ተከሰተ?
ጋዜጠኛው ጀማል ኻሾግጂ ከጎርጎሳውያኑ 2017 ጀምሮ በግዞት በአሜሪካ እየኖረ ነበር።
በጎርጎሳውያኑ ጥቅምት 2018 በኢስታንቡል በሚገኘው የሳኡዲ ቆንስላ ያመራውም እጮኛው ሃቲስ ሴንጊዝን ለማግባት የሚያስፈልጉትን መረጃዎች ለመውሰድ ነበር።
መርማሪዎች እንደሚያምኑት እዛው ገድለው አካሉንም እንደ ቆራረጡት ነው። አስከሬኑም ሆነ የተረፈ ነገር አልተገኘም። እጮኛው በወቅቱ ውጭ እየጠበቀች ነበር።
የሳዑዲ ባለስልጣናት በመጀመሪያ ከሳዑዲ ቆንስላ እንደወጣ የተናገሩ ሲሆን ከዚያ በኋላም በርካታ የሚጣረሱ መረጃዎች ሰጥተዋል።
ከዚያ በኋላ የወጣው የጋዜጠኛው አሰቃቂ አገዳደል ዝርዝር መረጃ አለምን አስደንግጧል። የተባበሩት መንግሥታትም የሳዑዲው ልዑል ቢን ሳልማንና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት በግድያው እጃቸው እንዳለበት የታመነ መረጃ እንዳለው ገልፆ ሪፖርት አወጣ።
ልዑሉ በግድያው ላይ እጄ የለበትም ብለው የካዱ ሲሆን ሆኖም " እንደ ሳዑዲ አረቢያ መሪነቴ ሙሉ ሃላፊነቱን እወስዳለሁ። በተለይም ገዳዮቹ ለሳዑዲ መንግሥት የሚሰሩ ከመሆናቸው አንፃር" ብለዋል።