ኮሮናቫይረስ፡ በዓለማችን ምርጥ የጤና ሥርዓት ያላቸው አምስቱ አገራት እነማን ናቸው?

የኮሮናቫይረስ ምርመራ በእስራኤል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዓለም ከኮሮናቫይረስ ጋር ፍልሚያ ውስጥ ገብታለች። የፍልሚያው ስኬት በአገራት የጤና አጠባበቅ ሥርዓት ውጤታማነት ላይ የተመሠረተ ይሆናል።

እስካሁን ባለው ሁኔታ ቫይረሱ በሰዎች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በመቀነስና መስፋፋቱን በመቆጣጠር በኩል አገራት ቀደም ሲል በዘረጉት የጤና ሥርዓት መካከል ግልጽ የሆነ ቁርኝት እንዳለ ባለሙያዎች ይስማማሉ።

በፈረንጆቹ 2019 መቀመጫውን ለንደን ባደረገው ተቋም የተጠናው 'ዘ ሌጋተም ፕሮስፐሪቲ ኢንዴክስ' በ12 መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ተመርኩዞ በ167 የዓለም አገራት ላይ ያደረገውን የምጣኔ ሃብት እና ብልጽግና ፖሊሲዎች እንዲሁም ተጨባጭ ሁኔታዎችን በመተንተን ደረጃ አውጥቷል።

የዚህ የሁኔታዎች አመልካች ዝርዝር ያስቀመጠው የጤና ሁኔታ ደረጃ በየአገራቱ ያሉ ሰዎች ምን ያህል ጤናማ እንደሆኑ እና የጤና ተቋማትን አገልግሎት የማግኘት ዕድል ላይ ተመረኮዞ የተዘጋጀ ነው።

በተጨማሪም በጤናው ዘርፍ ወደፊት ተራምደዋል የሚባሉት አገራት የኮሮናቫይረስን እንዴት እየተቆጣጠሩ እንደሆነ ለመገንዘብ የህክምና ባለሙያዎችንና የዜጎችን ምላሽ ሰብስቧል።

ጃፓን

የሩቅ ምሥራቋ አገር ጃፓን በመረጃ ጠቋሚው የጤና ዝርዝር ውስጥ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ላይ ትገኛለች። ኮቪድ-19ን በእንጭጩ ለመቆጣጠር በወሰደችው እርምጃ ብትወደስም የቫይረሱ ስርጭት መስፋፋት አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ እንድታውጅ አስገድዷታል። ቫይረሱን ሳይስፋፋ ለመቆጣጠር ባላት አቅም ምክንያት የመንቀሳቀስ እገዳ እንዳትጥል አድርጓታል።

ነዋሪዎች ያለምንም የቫይረሱ ምልክት የኮቪድ-19 ምርመራ ባይደረግላቸውም የሳምባ ምች ምርመራ ማደረግ ይችላሉ። "ይህም ታማሚው በፍጥነት ሕክምና እንዲያገኝ ያስችላል። ጃፓን ብዙ አስጊ ታካሚዎች የሌሏት ለዚህ ነው" ሲሉ መቀመጫቸውን በቶኪዮ ያደረጉት ዶክተር ሚካ ዋሺዮ ያስረዳሉ።

የጃፓናዊያን የጤና ግንዛቤ የኮቪድ-19 ተፅዕኖን ቀንሷል። "ቀድሞውንም ቢሆን ብዙ ጃፓኖች የፊት ጭንብል የማድረግና ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ዓመታዊ የጤና ምርመራ ማድረጋቸው አስከፊ ጉዳት እንዳይከሰት ረድቷል" ይላሉ።

ይህም ሆኖ ፈተና ሊደቀን ይችላል። ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች በተለመደው ሁኔታ ሆስፒታል መሆን ሲገባቸው መንግሥት ተጨማሪ ሃብት ለማሰባሰብ በሚል አልጋዎችን በከፍተኛ ደረጃ ለታመሙ እያስቀመጠ ነው ይላሉ ዋሺዮ።

የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ያደረገች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ደቡብ ኮሪያ

ደቡብ ኮሪያ ከፈረንጆቹ 2015 የሜርስ ወረርሽኝ ልምድ ኮቪድ-19ን ለመከላከል ዝግጁ ናት። ሆስፒታሎች ለዚህ በሚሆን መልኩ በባለሙያዎችና መሣሪያዎች ተዘጋጅተዋል።

51 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት አገር ከ450 ሺህ በላይ ሰዎችን ስትመረምር በቅርብ ጊዜ በየቀኑ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከ47 እስከ 53 ብቻ ነው።

የኮሪያ የጤና ሥርዓት ለዜጎች የጤና ኢንሹራንስን ስለሚሸፍን ለኮቪድ-19 ምርመራና ህክምና አስተዋጽኦ አድርጓል። "ምስጋና ለጤና ኢንሹራንስ እና ለመንግሥት ድጋፍ ይሁንና በአነስተኛ ዋጋ ምርመራው በስፋት ተካሂዷል" ሲሉ መቀመጫቸውን በሴኡል ያደረጉት ዶክተር ብራንደን ቢ ሱህ ተናግረዋል። "ወረርሽኙ እንደተከሰተ ብዙ ሰዎች ቀደም ብለው በመርመራቸው ተገቢው እርምጃ በወቅቱ ተወስዷል" ብለዋል።

መንግሥት እና ተቋማትም ውጤታማ የጤና እርምጃዎችን ለመተግበር በፍጥነት ተንቀሳቀሰዋል። "መንግሥት አዲስ እርምጃ በመውሰድ በጭምብል አቅርቦት ላይ በየቀኑ ሠርቷል" ይላሉ የሴኡል ሠራተኛው ዮንቦክ ሊ። "በብዙ ቦታዎች የሰውነት ሙቀት ይለካል። የኮሪያ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል እንዲሁም ሌሎችም የመንግሥት ተቋማት በግንባር ቀደምነት እየሠሩ ሲሆን ሕዝቡም ለጥረቶቻቸው ከፍተኛ አድናቆት እያሳየ ነው" ብለዋል።

መንግሥት ቀደም ተብሎ ጣልቃ መገባቱ ተስፋን ሰጥቷል። "ወረርሽኙ እየቀነሰ ሲሆን ሰዎች ሁሌም ጭምብል እያደረጉ ነው። ከቤት ውጪም እንቅስቀሴ ጀምረዋል" ብለዋል ሱህ።

ወረርሽኑ ከተስፋፋባቸው ቦታዎች አንዷ የሆነችው የዴጉ ከተማ ነዋሪዋ ዎን-ጄኦንግ ዋንግ ህይወት እንደቀደመው እየተመለሰ መሆኑን እየታዘቡ ነው።

እስራኤል

ኮቪድ-19 በዉሃን ሲከሰት በፍጥነት እርምጃ ከወሰዱ አገራት አንዷ እስራኤል ናት። ወረርሽኙ ከተከሰተ በሚል የጤና ሚንስቴር የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ድንጋጌን ጥር ላይ አጽድቋል።

በተለይም አስጊ ወደተባሉ አገራት አላስፈላጊ ጉዞ እንዳይደረግ እና ለይቶ ማቆያን ተግባራዊ ማድረጓ የወረርሽኙን ክስተት ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጓል።

እስራኤል ውስጥ ትክክለኛ ምርመራ በፍጥነት ተጀምሯል። ከመተንፈሻ አካላት ውስጥ ኮሮና ቫይረስን መለየት የሚያስችል አሰራር በአገሪቱ ቤተ-ሙከራዎች መዳረሱን የቴል አቪቭ ዩኒቨርሲቲው ባልደረባ ዶክተር ኪታም ሙህሴን ያስረዳሉ።"ከሚሊዮን ሰዎች መካከል ብዙዎችን በመመርመር ቀዳሚ ከሆኑት አገራት እስራኤል አንዷ ናት" ብለዋል።

"በምናደርገው የምርመራ ብዛት እኮራለሁ። ብዙ ቁጥር በመመርመራችን ነው ብዙ ሰው ቫይረሱ እንዳለበት ያወቅነው" ይላሉ የከፋር ሳባ ነዋሪው ታሊያ ክሌይን ፒሬዝ። "ሞት መጠኑ ዝቅተኛ የሆነው ቀደም ብለን ኳራንቲን ማድረግ በመጀመራችን ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።

በሕዝብ ላይ የተመሠረተ የጤና አጠባበቅ ሥርዓቱም ለተቀናጀ ምላሽ ምክንያት ሆኗል፡፡ "ወጪው ስለሚሸፈንላቸው ሰዎች የሕክምና ዕርዳታ ለማግኘት አይፈሩም" ሲሉ የእስራኤሉ ሼባ ሜዲካል ማዕከል ምክትል ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አርኖን አፌክ ገልጸዋል። "የህክምና ዋጋ ወሳኝ ነው። ምክንያቱም ሰዎች ምልክቶችን ሲያዩ በሽታውን ከማስፋፋታቸው በፊት ይታከማሉ።"

ለጤናው ዘርፍ በቂ ድጋፍ ከአጠቃላይ ኢኮኖሚው ባይደረግም ፈጣን እርምጃዎች ይወሰዳሉ ይላሉ አፌክ። "ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት ሁለት እርምጃ ቀድመን እንገኛለን። ታካሚዎች ሲመጡ ዝግጁ እንሆናለን" ብለዋል።

አንድ እስራኤላዊ በመንገድ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጀርመን

ጀርመን ከብዙዎቹ የአውሮፓ ጎረቤቶቿ አንፃር ሲታይ አነስተኛ የሞት ምጣኔ አላት። በዓለም አቀፍ ደረጃ ስኬታማ ብትባለም ባለሙያዎች ግን ሙሉ ለሙሉ ሥራውን አላጠናቀቀችም ይላሉ።

"በጀርመን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ምርመራና አነስተኛ የሞት ምጣኔው ለብዙዎች ግርምት እንዲሁም የአገሪቱን የጤና አጠባበቅ ደረጃ ያሳያል" ሲሉ ፕሮፌሰር ፍራንሲስ ደ ቬሪኮርት ገልጸዋል። ሰፊ ምርመራው ታማሚዎችንና ምልክት ያሳዩትን በመለየት ስርጭትን ለመቀነስ አግዟል።

አገሪቱ ጥንቃቄ ካላደረገች ይህ ዝቅተኛ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች መጠን አደጋ ሊያስከትል ይችላል። "አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እና ባህሪን መቀየር ቫይረሱ ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥር ስር እስኪውል ድረስ መቀጠል አለበት" ብለዋል ደ ቬሪኮርት።

ነዋሪዎች ነገሮች በቅርቡ ወደ ቀድሞው ሁኔታ ላይመለሱ ይችላሉ ቢሉም ተስፋ ግን አልቆረጡም። "በጣም የከበደኝ እናቴ ከቤት እንዳትወጣ ማድረግ ነው። ለዚህ ነው ጭንብል አዘጋጅቼ ከሦስት ሳምንት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አብረን ወደ ሱቅ የወጣነው" ሲሉ አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።

አክለውም "የአዳዲስ ተጠቂዎች ቁጥር በመቀነሱ ዕገዳዎችን በማላለቱ ዙሪያ ላይ ማስብ አስፈላጊ ይመስለኛል። የመንግሥት ኃላፊዎች በሽታውን እየተቆጣጠሩ ወደ መደበኛ ህይወታችን እንድንመለስ ይረዱናል ብዬ አምናለሁ" ብለዋል።

ውጤታማው የአገሪቱ የጤና ሥርዓት አገር አቀፍ ምላሽን ለማድረግ ዝግጁ ነው። "ብዙ አልጋዎች ፣በጣም ብዙ የጽኑ ህሙማን ክፍሎችና ብዙ ዶክተሮች አሉ። እነዚህን ለማስተዳደር ሁሉም የመንግሥት መዋቅር ኃላፊነት አለበት" ሲሉ ደ ቨሪኮርት አስረድተዋል።

አውስትራሊያ

አውስትራሊያ እንደ ጠቅላይ ሚንስትሯ ገለጻ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ፍጥነቱን ከአምስት በመቶ በታች አድርጋለች።

በአውስትራሊያ የመንግሥትና የግል በሆነው "ቅይጥ" የጤና አጠባበቅ ሥርዓቷ መጥፎ ሁኔታዎችን ለመቋቋም ተዘጋጅታለች።

ይህ በሁለቱ እገዛ የሚደረግ የጤና አጠባበቅ ሥርዓት አገሪቱን ዝግጁ እንዳደረጋት በሜልበርን ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር አሌክስ ፖልያኮቭ አስረድተዋል።

በተጨማሪም በአገር ውስጥ የቫይረሱ መተላለፍ ምጣኔ ዝቅተኛ ሲሆን፣ መንግሥትም ከውጪ ለመጡ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ በማዘጋጀትና በበሽታው ከተጠቁ ግለሰቦች ጋር ንክኪ ያላቸውን በፍጥነት እየለየ ነው።

"የአገር ውስጥ ስርጭት አነስተኛ ሲሆን በየዕለቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ እንደሚሆን እገምታለሁ። ይህ ነው ስርጭቱን መቆጣጠር ማለት" ብለዋል።

አሁን ባለው ፍጥነት ከቀጠለ አውስትራሊያ በቂ የጽኑ ህሙማን አልጋዎችና የመተንፈሻ መሣሪያዎች አሏት። "ከግል ሥርዓቱ የሚገኘው ተጨማሪ አቅም አብዛኛዎቹ ሰዎች ህክምና በወቅቱ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል" ብለዋል ፖልያኮቭ።

የእንቅስቃሴ ዕገዳዎች ከቀለሉ በኋላ ነዋሪዎች ወደ ቀድሞ ህይወታቸው ይመለሳሉ "ሁሌም በየሳምንቱ እንደምናደርገው ከጓደኞቼ ጋር እየሳቅን በምንወደው ካፌ ቡና መጠጣትን እናፍቃለሁ" ሲሉ መቀመጫቸውን ሲድኒ ያደረጉት የጉዞ ጸሐፊዋ ጄኒፈር ደ ሉካ ተናግረዋል።

ኮሮና
Banner