ዶናልድ ትራምፕ ‘ክትባት ተገኘም አልተገኘም እንቅስቃሴ እንጀምራለን’ እያሉ ነው

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ለኮቪድ-19 ክትባት ተገኘም፣ አልተገኘም አገሪቱ ወደ እንቅስቃሴ ትመለሳለች ብለዋል።

ክትባት ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ኒውክሌር መሣሪያ ለማግኘት ከተደረገው ሙከራ ጋር አነጻጽረውታል።

ፕሬዘዳንቱ፤ ለበሽታው ክትባት ባይገኝም እንኳን ዜጎች ወደመደበኛ ሕይወታቸው ይመለሳሉ ብለዋል።

የአሜሪካ የክትባት ምርምር

‘ኦፕሬሽን ራፕ ስፒድ’ የተባለው ፕሮጀክት 14 ተስፋ የተጣለባቸው የኮቪድ-19 የክትባት ምርምሮች ላይ እንደሚያተኩር ትራምፕ ትላንት በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

“አገራችን እንዲህ አይነት የሳይንስ፣ የኢንዱስትሪም ምርምር አድርጋ አታውቅም” ሲሉ ፕሮጀክቱን አወድሰዋል።

የቀድሞ የወታደርና የጤና ኃላፊ ከመንግሥትና ከግል ዘርፍ ጋር በመጣመር ፕሮጀክሩን ይመራሉ ተብሏል።

የክትባት ምርምር ዘርፉን የሚመሩት ሞንሴፍ ስላውኒ “በዚህ ዓመት መጨረሻ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ክትባቶች እንደምናመርት እተማመናለሁ” ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ከኒው ዮርክ ታይምስ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ክትባት ይገኛል ተብሎ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ አጭር ነው ብለው ነበር።

በርካታ ተመራማሪዎች እንደሚሉት፤ አሜሪካ ምጣኔ ኃብቷን ዳግመኛ ማንቀሳቀስ የምትችለው ክትባት ሲገኝ ነው።

ትራምፕ ግን “ሁሉም ነገር ክትባትን የተመረኮዘ ነው ብላችሁ እንድታስቡ አልፈልግም” ብለዋል። “ክትባት ቢገኝም፣ ባይገኝም ሂደቱን እየጀመርን ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።

“ብዙ በሽታዎች ክትባት ሳይገኝላቸው፣ ቫይረሱን ወይም ጉንፋኑን ሰዎች ይታገላሉ። አንዳንዶቹ በሽታዎች ደግሞ ክትባት እስከነጭራሹ ሳይገኝላቸው ይጠፋሉ” ብለዋል ፕሬዘዳንቱ።

ትራምፕ ትምህርት ቤቶች መከፈት አለባቸው ቢሉም፤ ኮሮናቫይረስ የመከላከል ግብረ ኃይልን የሚመሩት ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ ለዚህ ውሳኔ ገና እንደሆኑ ለምክር ቤቱ ቃላቸውን ሰጥተዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ትላንት መግለጫውን ሲሰጡ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል (ማስክ) አላደረጉም ነበር። አንዲት ጋዜጠኛ ጥያቄ ስታቀርብላቸው፤ ድምጿ በአግባቡ እንዲሰማ ያደረገችውን ጭምብል እንድታወልቅ አዘዋል።

በ2020 ለሽታው መፍትሔ ይገኛል?

ኢቦላ እአአ ከ2014 እስከ 2016 በተቀሰቀሰበት ወቅት የአሜሪካ የመድኃኒት ቁጥጥር ክፍል የመጀመሪያው ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል የፈቀደው በ2019 ነበር።

ከዋይት ኃውስ የሚወጣው የጊዜ ገደብ ላይ ብዙ የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ ያነሳሉ።

በባይለር ኮሌጅ የኮሮናቫይረስ ምርምር ላይ የሚሠሩት ዶ/ር ፒተር ሆቴዝ “ቢያንስ እስከ 2021 ድረስ ክትባቶች ፍቃድ ይሰጣቸዋል ብዬ አላስብም” ብለዋል።

ዶ/ር ሪክ ራይት የተባሉ የቀድሞ የአሜሪካ ክትባት ዘርፍ ዳይሬክተር፤ የኮሮናቫይረስ ሕክምና ላይ ከዋይት ኃውስ ፖለቲካዊ ጫና እየተደረገ ነው ሲሉ ቃላቸውን ለምክር ቤት ሰጥተዋል።