ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኮሮና ዘመን በኒው ዚላንድ ታሪክ የተፈፀመው ትልቁ የመኪና ዘረፋ
የሁሉም ዘራፊ 'ምኞት' ሳይሆን አይቀርም። በአንድ የመኪና አከራይ ኩባንያ ቅጥር ግቢ ውስጥ ጥሩ አቋም ያላቸው በርካታ ዘመናዊ መኪኖች ተሰልፈው ቆመዋል። የመኪኖቹ ቁልፍ ደግሞ መኪኖቹ ውስጥ ተንጠልጥሏል።
ኒው ዚላንድ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብን ጥላ ብትገኝም፤ ጥቂት ዘራፊዎች ግን ወደ ሥራ ተሰማርተዋል።
ዘራፊዎቹ ኒው ዚላንድ ኦክላንድ ከተማ የሚገኘውን ጁሲ የተባለ የመኪና አከራይ ድርጅት ሽቦ ቆርጠው ይዘልቃሉ። ከዛም እያንዳንዳቸው የሰረቁትን መኪና እያሽከርከሩ ይሄዱሉ።
ዘራፊዎቹ ዘረፋቸውን በመጀመሪያው ዙር አልቋጩትም። ደግመው ተመለሱ፤ እያሽከረከሩ ሄዱ። እንደገና ተመልሰው ተሰልፈው ከቆሙ መኪኖች እያመረጡ መውሰዳቸውን ቀጠሉ።
97 መኪኖች ከቆሙበት ተሰረቁ።
በአገሪቱ የእንቅስቃሴ ገደብ መጣሉን ተከትሎ፤ የኒው ዚላንድ ጎዳናዎች ጸጥ እረጭ ብለው ነበር። ፖሊስ ግን ጎዳናዎች ላይ ቅኝት ማደረጉን ቀጥሏል። በዚህ መሃል ፖሊስ በርካታ የኪራይ መኪኖች ሲሽከርከሩ ማየቱ ጥርጣሬን ፈጠረበት።
ፖሊስ መኪኖቹ መሰረቃቸው በማመኑ ለኩባንያው ያሳውቃል።
ብዙም ሳይቆይ በርካታ የኩባንያው መኪኖች የመሰረቃቸው ዜና የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን መነጋገሪያ ሆነ። ዜጎችንም መኪኖቹ እንዲገኙ ጥቆማ እንዲሰጡ ተጠየቁ።
ከተሰረቁት መኪኖች መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው መኪኖች በኢንተርኔት አማካኝነት ለመሸጥ ሲተዋወቁ ነበር። በሰዎች ጥቆማ እና በፖሊስ ጥረት ብዙም ሳይቆይ ከተሰረቁት 97 መኪኖች 85 ያክሉ ለአከራይ ኩባንያው ተመልሰዋል።
በአገሪቱ ታሪክ ትልቁ የመኪና ስርቆት ከተባለለት ወንጀል ጋር በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ግንኙነት አላቸው የተባሉ 29 ሰዎችም በቁጥጥር ሥር ውለዋል።