ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ልደት፣ ሠርግ እና ሞት በኮሮናቫይረስ ዘመን
ዶ/ር ሺላ አቲኖ (ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ስሟ ተቀይሯል) ብዙ ልጆች አዋልዳለች።
በቅርቡ ህክምና መስጫ ውስጥ ያገኘቻት ነፍሰ ጡር ግን ከሌሎቹ ትለያለች። የ32 ሳምንት ነፍሰ ጡር የነበረችው ሴት ኮሮናቫይረስ ከተገኘባቸው ኬንያውያን አንዷ ናት።
ናይሮቢ የሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ሴቲቱን ለማዋለድ ከተመረጡ ዶክተሮች አንዷ የሁለት ልጆች እናቷ ሺላ ናት።
“ቫይረሱ ያለባትን ሴት አንደማዋልድ ማወቅ እጅግ ከባድ ነው” ትላለች።
ነፍሰ ጡሯን ለማዋለድ ቀዶ ህክምና ማድረግ ነበረባት። ህክምናውን ስታደርግ ሰውነቷን ብትሸፍንም፤ ከነፍሰ ጡሯ ሴት ሰውነት ፈሳሽ እንደሚወጣና ንክኪ ሊኖር እንደሚችል ማሰብ አስጨንቋታል።
“ህክምናውን ጨርሼ ቤቴ ስገባ ልጆቼ ሊያቅፉኝ እጃቸውን ይዘረጋሉ፤ ልብሴን አውልቄ እስክታጠብ ድረስ ግን አልጠጋቸውም።” ይሄ በአካልም በመንፈስም ያደክማል። ወረርሽኙ ኖረም አልኖረም ህጻናት ወደዚህ ዓለም ሲመጡ መቀበል ሥራዬ ስለሆነ አማራጭ የለኝም።”
አዲሶቹ ሙሽሮች
ፍራንሲስ እና ቬሮኒካ አዲስ ሙሽሮች ናቸው። ኒያሁሩ በተባለ የኬንያ ግዛት የጫጉላ ሽርሽር እያደረጉ ነው።
500 ዘመድ አዝማድ የሚታደመው ሠርግ ደግሰው ነበር። ያልጠበቁት ደርሰና በኮሮናቫይረስ ምክንያት ዓለም እንዳልነበረች ሆነች።
ጥንዶቹ እንዳሰቡት 500 ሰው አልጠሩም። ስድስት ሰው ብቻ በተገኘበት በቤተ ክርስትያን ተጋቡ።
ቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው ሠርጉ ላይ መታደም አልቻሉም።
ጥንዶቹ ኮቪድ-19 ስጋት መሆኑ ሲያበቃ መጋባት ይችሉ ነበር። ነገር ግን “የፈጣሪ ፍቃድ ነው” ብለው ሠርጋቸውን በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች በተገኙበት ማድረጋቸውን ይናገራሉ።
“እኔና ቬሮኒካ እንዋደዳለን። መጋባት የምንፈልገው በፈጣሪ ፊት ነው” ይላል የቤተ ክርስቲያን አገልጋዩ ፍራንሲስ።
ሠርጋቸው 300 ሺህ የኬንያ ሽልንግ ይፈጃል ተብሎ ነበር። ስድስት ታዳሚ ብቻ ሲኖረው ግን 50 ሺህ ሽልንግ እንዳወጡ ሙሽራው ይናገራል።
“ብዙ ወጣት ጥንዶች እየደወሉልን ነው። ድል ያለ ድግስ ደግሰን እዳ ውስጥ ከምንገባ እንደናንተ በቀላል ሠርግ ለመጋባት ወስነናል ብለውናል።”
ሀዘን ያጠላበት ቤተሰብ
ኬንያ የሰዓት እላፊ ገደብ ጥላለች።
የአገሪቱ ፖሊሶች ይህን ገደብ ለማስጠበቅ ሲዘዋወሩ ያሲን ሁሴን ማዮ የተባለ የ13 ዓመት ታዳጊ መገደሉ ይታወሳል።
የሰዓት እላፊ ገደቡ ከታወጀ በኋላ በመላው አገሪቱ በፖሊስ እንግልት የደረሰባቸው ብዙዎች ናቸው።
የያሲን አባት ሁሴን ማዮ “ቀን ቫይረሱ ያሰጋናል፤ ማታ ደግሞ ፖሊሶች ያሸብሩናል” ሲሉ የልጃቸው ቀብር ላይ ተናግረዋል።
በተለያዩ ኢ-መደበኛ ዘርፎች የተሰማሩ አቅመ ደካማ ኬንያውያን ጭንቅ ውስጥ ናቸው። አንድም በኮሮናቫይረስ በሌላ በኩል ደግሞ በረሀብ እና ፖሊስ በሚሰነዝርባቸው ጥቃት።
መሳለቂያ የሆኑት ፖለቲከኛ
ጄምስ ኦሬንጎ የተቃዋሚው ኦሬንጅ ዴሞክራቲክ ፓርቲ አባል ናቸው።
“መኪናዬን እያሽከረከርኩ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ለማድረግ ሄድኩ” ብለው ፖለቲከኛው ትዊት ማድረጋቸው በበርካቶች አስተችቷቸዋል።
“እነዚህ ፖለቲከኞች የራሳቸውን መኪና መንዳት ያስገርማቸዋል እንዴ?” ሲሉ ብዙ ኬንያውን በፖለቲከኛው ተሳልቀዋል።
ሕዝቡ በወረርሽኙ ሰበብ ጭንቅ ውስጥ ሳለ መኪና መንዳታቸውን ከሚገባው በላይ ያዳነቁት ፖለቲከኛ፤ የብዙሀኑ እውነታ ግድ የማይሰጣቸው ፖለቲከኞች ምሳሌም ተደርገዋል።
እድለኛው እስረኛ
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መሰራጨቱን ተከትሎ በኬንያ ፍርድ ቤቶች ችሎት በዲጂታል መሣሪያዎች እየተካሄደ ነው። መንግሥት የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ከሳለፋቸው ውሳኔዎች አንዱ እስረኞችን መፍታትም ነው።
በዚህ ወቅት ፍርድ ቤት ከቀረቡ አንዱ ከመደብር መጽሐፍ ቅዱስ በመስረቅ ተከሶ የነበረው ግለሰብ ነው። እድለኛው እስረኛ ክሱ የተነሳለት ሲሆን፤ መንግሥት 4,800 እስረኞችንም ፈቷል።
መጽሐፍ ቅዱስ በመስረቅ የተከሰሰው እስረኛ ነፃ ወጥቶ፤ የኮሮናቫይረስ ስርጭት እንዲቆም መጽሐፍ ቅዱስ ይዘው እየጸለዩ ያሉ ኬንያውያንን ተቀላቅሏል።
(ይህ ጽሑፍ በጆሴፍ ዋሩንጉ ተጽፎ፤ “ሌተርስ ፍሮም አፍሪካን ጆርናሊስትስ” የተባለውና የአፍሪካ ጋዜጠኞችን ጽሑፍ የሚያስተናግደው አምድ ላይ የወጣ ነው።)