ኮሮናቫይረስ ፡የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ ባንክ እያዘጋጀሁ ነው አለ

አዲስ አበባ

የፎቶው ባለመብት, Sean Gallup

የኮሮናቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከተሰማበት ዕለት አንስቶ መንግሥት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ይረዳኛል ያላቸውን በርካታ እርምጃዎች ሲወስድ ቆይቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በከተማዋ ያለውን ሥርጭት ለመግታት ከውጭ ለሚመጡ ተጓዦች የለይቶ ማቆያ ቦታ ማዘጋጀትን ጨምሮ ሌሎች ሥራዎችንም ሲሰራ ነበር።

ከእነዚህ ሥራዎች ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ፅ/ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ወ/ሪት ፌቨን ተሾመ የከተማዋ ባለሃብቶች፣ ግለሰቦችና ወጣቶች የከንቲባውን ጥሪ ተከትሎ በርካታ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

ድጋፉ የገንዘብ፣ የቁሳቁስ እንዲሁም የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ነበር ያሉት የፕሬስ ሴክረተሪዋ እስካሁን ከ200 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የገንዘብና የአይነት ድጋፍ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

የተሰባሰቡት የንጽህና መጠበቂያዎች አቅም ለሌላቸው የከተማዋ ነዋሪዎችን በየክፍለ ከተማው በመለየት የመስጠት እንቅስቃሴ በዚህ ሳምንት ይጀመራል ያሉት ወ/ት ፌቨን፣ በየክፍለ ከተማው ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ተብሎ ከ450 ሺህ በላይ ዜጎች መለየታቸውንም ጨምረው አስረድተዋል።

በሌላ ዓለም እንደታየው የቫይረሱ ሥርጭት ከፍ ካለ እና ዜጎች ተንቀሳቅሰው መስራት የማይችሉበት ነገር ከተፈጠረ በማለት የከተማ አስተዳደሩ የምግብ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱንም ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ጠቁመዋል።

በዚህም መሰረት በየወረዳው ከ1 ሺህ 20 በላይ የምግብ ማከማቻና ማሰራጫ ማዕከላት እየተደራጁ ነው በማለት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች የመለየት ሥራም ተከናውኗል።

ፕሬስ ሴክሬታሪዋ እንዳሉት በእነዚህ በተዘጋጁት ማዕከሎች በኩል ግዢ የተፈፀመባቸው እህሎችንና ሌሎች ቁሳቁሶች የማስገባት ሥራ ተጀምሯል።

በከተማዋ የሚገኙ በርካታ ግለሰቦች የመኖሪያ ቤታቸውን፣ የእምነት ተቋማት የአምልኮ ሥፍራቸውን እንዲሁም ሆቴሎች ቦታቸውን ለለይቶ ማቆያነት ለመስጠት ቃል መግባታቸውን አስታውሰው፤ የከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ሥፍራዎች ለለይቶ ማቆያነት እንዲሆኑ ለማድረግ በቁሳቁስ የማሟላት ሥራ እየተከናወነ ነው።

እነዚህን ሥፍራዎች ውስጥ አልጋ፣ ፍራሽ፣ አልባሳት እንዲሁም የሕክምና አገልግሎት እንዲሟላላቸው የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኮሮና
Banner