ኮሮናቫይረስ፡ ከዚህም በላይ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ተገለጸ

የኢትዮጵያ መንግሥት በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ነው ሲል በማስታወቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደነገገ።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጻፈው ይህ መግለጫ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ግልጽ አላደረገም።

መግለጫው መንግሥት ችግሩን በደረሰበት ልክ ለመቋቋም ተዘጋጅቷል ያለ ሲሆን ውሳኔውንም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 መሰረት መታወጁን ገልጿል።

"አገርን ለማዳንና ትውልድን ለመታደግ ከዚህ በላይ እርምጃ ልንወስን እንደምንችልም መታወቅ አለበት" ያለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ፣ ዜጎችንም ከዚህ በላይ ግዴታቸውን ለመወጣት መዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስቧል።

በዚህ ወቅት ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ችግሩን ለመቋቋም ከሚሠሩት አካላት ጋር አብሮ እንዲቆም የጠየቀው ይህ መግለጫ ከዚህ በተቃራኒ ችግሩን ለማባባስ የሚሠሩ ካሉ ግን፣ "በሕጉ መሠረት የማያዳግም ርምጃ እንወስዳለን" ሲል ያስጠነቅቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ መግለጫቸው ላይ አክለውም ለተቸገሩ ወገኖች እገዛ እንዲደረግ እንዲሁም የቤት አከራዮች የተከራዮችን እዳ እንዲከፍሉ ጥሪ አቅርበዋል።

"ከቻልን አናስከፍላቸው፤ ካልቻልን ቅናሽ እናድርግላቸው። ያም ካልሆነ ይህ ጊዜ እስኪያልፍ እንታገሣቸው። በዚህ ወቅት ተከራዮችን ከቤት ማስወጣት ፈጣሪም፣ ታሪክም ሕግም ይቅር የማይሉት ወንጀል ነው።"

በማለት "ማናችን አልፈን ማናችን እንደምንተርፍ ለማናውቅበት ጊዜ ከመተባበር የተሻለ መሻገሪያ የለንም" ብለዋል።

በተጨማሪም ለግል ባለሀብቶች የሠራተኞቻቸው ሕይወት እንዳያስጨንቁ አደራ ብለዋል።

መንግሥት የኢኮኖሚ ችግሮችን ለመፍታት አስፈላጊውን ሁሉ እየወሰነ አብሯችሁ እንደሚሆን በዚህ አጋጣሚ እገልጥላችኋለሁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተለያዩ አካላት እያደረጉ ስላሉት አገልግሎት ምስጋና እንደሚገባቸው ገልፀዋል።

ለሕክምና ባለሞያዎች ተገቢውን ሁሉ አለማድረግ እጅን በእጅ እንደመቁረጥ በማለትም እነዚህን ባለሞያዎች በሚቻለው ሁሉ መርዳት እንደሚገባ ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ፣ ያለ እነርሱ ግንባር ቀደምነት ትግሉን ልናሸንፍ አንችልም ብለው፤ "የሕክምና ባለሞያዎችን ማክበር፣ ማመስገንና በጉዟቸው ሁሉ መተባበር ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል።"

አክለውም የመከላከያ አባላት፣ የፖሊስ ሠራዊት አባላት፣ የኤሌክትሪክ ኃይልና የውኃ አቅርቦት እንዳይስተጓጎል የሚሠሩ ባለሞያዎች፣ የሚዲያ ባለሞያዎች፣ የመገናኛ መሥመሮቻችን ላይ 24 ሰዓት የሚያገለግሉ ዜጎች፣ ተገቢው ምስጋናና ድጋፍ ከቤተሰባቸውም፣ ከማኅበረሰባቸውም ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

ከቫይረሱ ባልተናነሰ የእርሻ ምርት መቀነስና የእርሻ ምርት አለመኖር ሀገራችንንና ሕዝቧን ይጎዳል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግብርና ስራ ላይ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች "እናንተ ሀገር መጋቢዎች ስለሆናችሁ፣ እየተጠነቀቃችሁ ካለፈው የተሻለ ምርት ለማምረት ትጉ" ሲሉ መክረዋል።

እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርቶቻችንም ፈጽመው መቆም የለባቸውም ሲሉ አረጋግጠዋል።

በተለይም ከውጭ የምናመጣቸውን ምርቶች ለመተካት ለሚደረገው ጥረት መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግላችሁ እገልጥላችኋለሁ በማለትም ለአጠቃላእ ማህበረሰብ የሚሰጤጡ ምክሮችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አስታውሰዋል።

በመጨረሻም "በኮሮና አይቀለድም፤ ጉዳዩ ከመኖርና ካለመኖር ጋር የተያያዘ ነው" በማለት አጠናቅቀዋል።