"ምርጫ ቦርድ የሄደበት መንገድ ትክክል አይደለም" ኦነግ እና ኦፌኮ

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ቀጣዩን ምርጫ የመሰረዝ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የሄደበት መንገድ ትክክል አይደለም ሲሉ የኦሮሞ ነጻነት ግንባርና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ገለጹ።

ሁለቱ ድርጅቶች ባወጡት የጋራ መግለጫ ላይ እንዳሉት "ኮቪድ-19 በምርጫ 2012 እቅድና የጊዜ ሰሌዳ አፈጻጸም ላይ ተግዳሮቶችን ደቅኖ ቦርዱን እየተፈታተነ መሆኑን" እንደሚረዱ አመልክተው፤ ነገር ግን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ "የሄደበት መንገድ ትክክል አይደለም ብለን እናምናለን" ብለዋል።

ጨምረውም ቦርዱ ከዚህ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ መጋቢት 12 ቀን 2012 ዓ.ም ገዢውን ፓርቲ ጨምሮ የኦሮሞ ነጻነት ግንባርና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) የተገኙበት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰብስባ አዘጋጅቶ ምክክር ተደርጎ እንደነበር ጠቅሶ፤ በስብሰባው መጨረሻ ላይ ሌላ ዙር ወይይት እንደሚኖር ቢገለጽም ይህ ሳይሆን ውሳኔ ላይ መድረሱ አግባብ አይደለም ብሏል።

ነገር ግን ወረርሽኙ በሁሉም ዘርፍ የሚያስከትለውን ችግር ለማስወገድ ቅድሚያ በመስጠት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸው፤ ከዚሁ ጎን ለጎን ለቀጣዩ ምርጫ ለመዘጋጀት አስፈላጊው ሁሉ እንዲደረግ ፓርቲዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም ምርጫውን በተመለከተ ቀጣይ እርምጃ ለመውሰድ ሁሉም ባለድርሻ አካላት መሳተፍ እንዳለባቸው ፓርቲዎቹ አመልክተዋል። ከዚህ ውጪ"ምርጫውን ማራዘምና ቀጣዩ የአገሪቱን ዕጣ ፋንታ ለመወሰን መሞከር የባሰ አገራዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል" በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።

መግለጫው በተጨማሪም አገሪቱ አሁን ባለችበት ሁኔታ ውስጥ "ምርጫውን የማራዘም ውሳኔም ሆነ ከመስከረም 2013 በኋላ ሊኖር የሚችልን መንግሥት መወሰን አሁን ላለው መንግስት ብቻ የሚተው ጉዳይ አይደለም" በማለት ጉዳዩ አጠቃላይ አገራዊ ተሳትፎን እንደሚፈልግ ጠቅሷል።

ከበሽታው ጋር በተያያዘም ወረርሽኙን ለመግታት ተብለው በመንግሥት የሚወጡ ሕጎች፣ ደንቦችና ውሳኔዎች "እየጠበበ የመጣውን የተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ የባሰ ለማጥበብ መንግሥት እንዳይጠቀምበት ቁጥጥር ማድረግና አላስፈላጊ የሆኑ ሕጎችን ከማውጣት" እንዲቆጠብ ጠይቀዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ወረርሽኙኝን የሚመለከቱ መመሪያዎችና መልዕክቶችን በዋናነት ለሕዝብ ጤና ጥበቃ ተቋማትና ባለሙያዎች እንዲተዉ አሳስበዋል።

በማጠቃለያ ላይም ምርጫውን ለማራዘምም ሆነ በቀጣይ እርምጃ ላይ መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቭክ ማኅበራትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገናኝተው ተከታታይ ውይይትና ምክክር በማድረግ ሁሉም አማራጭ ሃሳቦች ማቅረብ እንዲችል መንግሥት ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል።