ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ የአፍሪካ አገራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እየደነገጉ ነው
ሴኔጋልና አይቮሪኮስት በግዛቶቻቸው ውስጥ የኮሮናቫይረስ መስፋፋትን ለመግታት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግ ሌሎች የአፍሪካ አገራትን ተቀላቀሉ።
የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል እንዳስታወቁት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ የሚሆነው ዛሬ ማክሰኞ ዕኩለ ሌሊት ላይ ሲሆን ከምሽቱ 2 ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት የሚቆይ የሰዓት እላፊም ተጥሏል።
የአገሪቱ ጦር ሠራዊትና ፖሊስ የተላለፉትን ውሳኔዎች እንዲያስፈጽምም ታዟል።
ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ይህንን እርምጃ ያስታወቁት አገራቸው የበሽታውን መስፋፋት ለመግታት ፈተና ውስጥ እንደሆነች ለሕዝባቸው ዛሬ ባደረጉት ንግግር ነው።
"በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የመጀመሪያው ታማሚ ከተገኘ በኋላ መንግሥት ወረርሽኙን ለመግታት አስፈላጊውን ጥረት ያደረገ ቢሆንም፤ እስካሁን ያሰብነውን አላሳካንም" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
በሴኔጋል እስካሁን በኮሮናቫይረስ አማካይነት በሚተላለፈውና ኮቪድ-19 በተባለው የመተንፈሻ አካላት ወረርሽኝ መያዛቸው የተረጋገጠ 79 ሲሆን ከእነዚህም መካከል 8ቱ ሰዎች ድነዋል።
በአገሪቱ በሽታው ከተገኘባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ ነበራቸው የተባሉ ከ1500 በላይ በሚሆኑ ሰዎች ላይ ክትትል እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም ለበሽታው መቆጣጠሪያ 1.5 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ለአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታ ደግሞ 80 ሚሊዮን ዶላር የተመደበ መሆኑንና ተናግረዋል።
የአይቮሪኮስት ፕሬዝዳንት አሌሳኔ ኦታራ ደግሞ መንግሥታቸው ከዛሬ ምሽት 3 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋት 11 ሰዓት የሚቆይ ሰዓት እላፊ በማወጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቀስ በቀስ ተግባራዊ መሆን እንደሚጀምር አሳውቀዋል።
"በገጠመን የወረርሽኝ መስፋፋት ምክንያት በመላዋ አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲደነገግ ወስኛለሁ" ሲሉ ፕሬዝዳንቱ በቴሌቪዥን ቀርበው መናገራቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል።
ፕሬዝዳንት ኦታራ በተጨማሪም ከሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ወደ ዋና ከተማዋ የሚደረጉ ያልተፈቀዱ እንቅስቃሴዎች እንዳይደረጉና መጠጥ ቤቶችም እንዲዘጉ አዘዋል።
በበሽታው መስፋፋት ምክንያት ቀደም ብለው የአስቸኳይ ጊዜ ያወጁ ሌሎቹ የአፍሪካ አገራት ሱዳን፣ ግብጽና ሊቢያ ናቸው።