የቀድሞው የደኅንነት መስሪያ ቤት ምክትል ይናገራሉ

አቶ ወልደሥላሴ ወልደሚካኤል በ1972 ዓ.ም ወደ ህወሓት የትጥቅ ትግል የተቀላቀሉ ሲሆን ከደርግ ውድቀት በኋላ ደግሞ በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ተቋም ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ አገልግለዋል። በሙስና ተጠርጠረው ከተቋሙ በ2003 ዓ.ም እስከወጡበት ጊዜ ድረስ የአገር ውስጥ መረጃና ደኅንነት ኃላፊ ሆነው ሠርተዋል። እነሆ ከቢቢሲ ጋር የነበራቸው ቆይታ. . .

እርስዎ በደኅንነት ተቋሙ ውስጥ በነበሩበት ወቅት መስሪያ ቤቱ በትግራይ ተወላጆችና ህወሓት አባላት የተያዘ ነው ይባል ነበር። ምን ይላሉ?

አቶ ወልደሥላሴ፡ የተቋሙ ግዙፍ ክፍል በሆነው የአገር ውስጥ መረጃና ደኅንነት ኃላፊ በመሆን ነው ረጅም ጊዜያት ያሳለፍኩት። ስለዚህም በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ውስጥ የነበረውን አጠቃላይ የሠራተኞችን ብዛት ያየን እንደሆነ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት የአማራ ብሔር ተወላጆች ናቸው። ቀጥሎ ደግሞ የኦሮሞና የትግራይ ተወላጆች ቁጥር ተቀራራቢ ነው። ይህን መረጃ ከተቋሙ የሰራተኞች ፋይል በቀላሉ ማረጋገጥ የሚቻል ነው። በመሰረቱ ይህ አጀንዳ በተደጋጋሚ ይነሳ ስለነበር ጥናት አካሂደንበታል።

ታድያ ሐቁ ይህ ከነበረ ለምንድነው ተቋሙ በትግራይ ተወላጆች እንደተሞላ ጥያቄ ሲነሳበትና በጥርጣሬ ሲታይ የነበረው?

አቶ ወልደሥላሴ ወልደሚካኤል፡ በታሪክ አጋጣሚ ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ በዘርፉ የተሻለ ተሞክሮና ትምህርት የነበራቸው ከህወሓት ይበዙ ነበር። ከዚህ የተነሳ እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ በኃላፊነት ደረጃ ከነበሩት ሰዎች አብዛኞቹ የትግራይ ተወላጆች ነበሩ። ነገር ግን ከዚያ በኋላ በኃላፊነት ያሉትም ሰዎች መመጣጠን አለበት ተብሎ የማመጣጠን ሥራ ተከናውኗል። ከላይ ለማስመቀመጥ የሞከርኩት ግን ከተቋሙ አጠቃላይ ስታፍ [የሰው ኃይል] አንጻር ያለውን ብዛት ነው።

ሌላኛው በጥራጣሬ ዓይን ይታይ ነበር የተባለውን ግን እኔ አልቀበለውም። ምክንያቱም በምንሰራቸው ሥራዎች በሙሉ የሕዝቡ ተሳትፎ የላቀ ስለነበረ ነው። አብዛኞቹ አገሪቱን የማተራመስ ህቡዕ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ሕዝቡ ቀድሞ መረጃ በመስጠት ይተባበረን እንደነበር አስረግጬ ልነናገር እችላለሁ።

ኢትዮጵያ ተጋርጠውባት የነበሩት የደኅንነት አደጋዎችና እነዚህን በማክሸፍ ረገድ የሕዝቡና መንግሥትን ሚና በመጽሐፌ በስፋት ገልጬዋለሁ። የደኅንነት መስርያ ቤቱ በደርግ ግዜ በጣም ተፈሪ ነበር። በኋላ ግን የሚያስመካ እምርታ አስመዝግቧል ባልልም እንኳ በደርግ ጊዜ ከነበረው እጅግ የተሻለና ሕዝብ ወዶ የሚተባበረው ተቋም ነበር ማለት ግን እችላለሁ።

የደኅንነት ተቋሙ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሲፈጽም እንደነበር በስፋት ሲነገር ቆይቷል። ከዚህ አንጻርስ ምን ይላሉ?

አቶ ወልደሥላሴ ወልደሚካኤል፡ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጊዜ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በተለያዩ ዘርፎች ጉልህ ጉድለቶች እንደነበሩና ለዚህ ደግሞ ዋናው ተጠያቂ ራሱ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ እንደሆነ ገምግሟል።

ስለዚህ ከዚህ በመነሳት የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እንደየተልዕኳቸው በሰብአዊ መብት ረገጣ የየራሳቸውን ድርሻ ይወስዳሉ ማለት ነው። እውነት ለመናገር የአገሪቷን ደኅንነት ለማረጋገጥ ተብሎ በሰብአዊ መብት አያያዝ በኩል ጉድለቶች ሊኖሩ ይችላሉ። እኔ እስከማውቀው ድረስ ግን የደኅንነት ተቋሙ የዜጎችን ህይወት እና ንብረት ለመጠበቅ በታታሪነት ይስራ የነበረ ተቋም ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በመገናኛ ብዙሃን በወንድ ብልት ላይ ውሃ ማንጠልጠልና ጥፍር እስከመንቀል የደረሱ በደሎች ተፈጽሞብናል የሚሉ ሰዎች ቀርበው ታይተዋል። የደኅንነት ተቋሙ በዚህ ውስጥ እጁ የለበትም?

አቶ ወልደሥላሴ ወልደሚካኤል፡ የአገሪቱ የደኅንነት መስሪያ ቤት ሥራው መረጃ ማሰባሰብ ነው። መረጃ አሰባስቦ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ያቀርባል። ከዚያ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያገኘውን መረጃ ተንተርሶ ከሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ጋር ሆኖ እርምጃ በመወስድና ባለመውሰድ ላይ ይወስናል።

እኔ በተቋሙ በኃላፊነት ደረጃ እስከነበርኩበት እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ መረጃ በምርመራ የማግኘት ኃላፊነት የተሰጠው የፌደራል ፖሊስና የክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች ነው።

ስለዚህ የመረጃና ደኅንነት ተቋሙ ሥራና ኃላፊነት የነበረው የሕዝቡን አቅም ተጠቅሞ መረጃ በማሰባሰብ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል መስጠት ነው። ሥራው ራሱ በሕግ የተወሰነ ነው። የምርመራ ሥራ የእኛ ሥራ ስላልነበረ ከዚህ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጉዳዮች ለእኔ ግልጽ አይደሉም።

ስለዚህ ተፈጸሙ የተባሉት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በየትኛው የመንግሥት አካል ነው የተፈጸሙት?

አቶ ወልደሥላሴ ወልደሚካኤል፡ መረጃው የለኝም።

በሙስና ተጠርጥረው ታስረው እንደነበር ይታወሳል። የቀረበብዎን ክስ ተቀብለውታል?

አቶ ወልደሥላሴ ወልደሚካኤል፡ በእኔ የሙስና ክስ ጉዳይ እኔ ባለጉዳዩ ከምናገረው በላይ ከእራሱ ከፍርድ ቤቱ ብትጠይቅ ነው የሚሻለው።

በእርስ በኩልስ ግን ተቀብለውት ነበር?

አቶ ወልደሥላሴ ወልደሚካኤል፡ ክሶቹ መሰረተ ቢስ ስለነበሩ አልተቀበልኳቸውም፤ ፍርድ ቤቱም ሁሉንም ውድቅ አድርጓቸዋል። በሁለት ክሶች ግን አልከላከልም ብዬ አልተከላከልኩም።

አንደኛው ክስ ሽጉጥና ጠብመንጃ ተገኝቶብሃል የሚለው ነው፤ በነበረኝ የሥራ ኃላፊነት የተነሳ ለምን እንደያዝኩት የሚታወቅ ስለሆነ ለመከላከል ሞራሌ አልፈቀደልኝም። ሁለተኛው ደግሞ በሥራ ምክንያት እንደሆነ እየታወቀ ለአንዲት ሴት የትራስፖርት አገልግሎት ትሰጥ ነበር ተብሎ የቀረብኝን ክስም አልከላከልም ብያለሁ። ታዲያ የተቀጣሁትም በእነዚህ ሁለት ክሶች ነው።

በተረፈ ሌሎቹን ማለትም መጽሐፍ አሳትሞ ሲሸጥ ስልጣኑን ይጠቀም ነበር የሚለውንና በአዲስ አበባ ምንጩ ባልታወቀ ገንዘብ ቤት ገንብቷል ተብለው ለቀረቡብኝ ክሶች አስፈላጊውን መረጃዎችን አቅርቤ ፍርድ ቤት ነጻ ብሎኛል።

ተከሰው ሲታሰሩ እኮ ከደኅንነት መስርያ ቤቱ ለቀው ነበርና በሚታወቅ የሥራ ባህሪ ምክንያት ነው መከላከል ያልፈለግሁት ያሉት አይጋጭም?

አቶ ወልደሥላሴ ወልደሚካኤል፡ የጠብመንጃውና የሽጉጡ ጉዳይን ለማለት?

አዎ

አቶ ወልደሥላሴ ወልደሚካኤል፡ ለምን ሽጉጥና ጠብመንጃ እንደያዝኩ፣ ለምን መኪና እንዳሰማራሁ ለማብራራት የሥራው ባህሪና ዲሲፕሊን አይፈቅድልኝም።

ሲታሰሩ ግን የትግራይ ልማት ማኅበር የቦርድ ሊቀ መንበር ነበሩ አይደል ?…

አቶ ወልደሥላሴ ወልደሚካኤል፡ የትግራይ ልማት ማኅበርን ሥራ እሰራ የነበረው በተደራቢነት እንጂ በቋሚነት አልነበረም። ከመታሰሬ ከሁለት ወር ገደማ በፊት ከሥራ ኃላፊነቴ እንደተነሳሁና ሌላ ሥራ ምድባ እየተጠባበኩ ሳለሁ ነበር የታሰርኩት።

የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዋና ኃላፊ የነበሩትን አቶ ጌታቸው አሰፋን እንዴት ይገልጿቸዋል? በመካከላችሁስ ምን አይነት ግንኙነት ነበረ?

አቶ ወልደሥላሴ ወልደሚካኤል፡ የነበረው ኃላፊነትና የሥራ ባህሪ ምን እንደነበር ይታወቃል። እንደዚህ አይነት የሥራ ባህሪ ያለውን ተቋም ይመራ የነበረን ሰው ሥራው በሚድያ ወጥቶ መገምገም ፍትሐዊ ነው ብዬ አላምንም። በተጨማሪ ደግሞ እኔ በምሰጠው አስተያየት ላይ ምላሽ በማይሰጥበት ሁኔታ፤ ለዚያውም በዚህ ጊዜ መናገሩ ደግሞ አስፈላጊ አይደለም ባይ ነኝ።

በአሁኑ ወቅት የት ነው ያሉት? ምንስ እየሰሩ ነው?

አቶ ወልደሥላሴ ወልደሚካኤል፡ የማስተማር ፍላጎት ስለነበረኝ ከዚህ በፊት ከሥራዬ ጎን ለጎን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ አስተምር ነበር። የአክሱም ዩኒቨርስቲ መምህራንን ለመቅጠር ባወጣው ማስታወቂያ መሰረት ተወዳድሬ በፖለቲካል ሳይንስ ትምህርት ክፍል እያስተማርኩኝ ነው።

ከእስር ቤት እንደወጡ በቀጥታ ወደ ትግራይ ነበር የሄዱት፤ በዚህም የማዕከላዊው መንግሥት 'ሰላይ' ሆነው እንደሄዱ ይወራ ነበር፤ በዚህ ላይ ምላሽዎ ምንድን ነው?

አቶ ወልደሥላሴ ወልደሚካኤል፡ ይህ እንኳን ድካም ነው። እንደተባለውም ወሬ ነው ሊሆን የሚችለው፤ ሆን ተብሎ የተወራም ሊሆን ይችላል። ከድንቁርና የሚመነጭ ወሬ ስለሆነ በዚህ ላይ ጊዜያችንን ባናጠፋ ጥሩ ነው።

እንደቀድሞ የአገሪቱ የመረጃና ደኅንነት ሹም አሁን ያለውን ተቋም እንዴት ትገመግመዋለህ?

አቶ ወልደሥላሴ ወልደሚካኤል፡ እውነት ለመናገር መረጃው የለኝም። ምን ዓይነት ፈተናዎች እየገጠሟቸው ነው? እነዚያን ፈተናዎች ቀድመው እየደረሱባቸው ነው ወይ? እንዴት አድርገውስ በአነስተኛ ዋጋ እየመከቷቸው ነው? የሚሉ መረጃዎች ስለሌሉኝ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ለማውራት ይከብደኛል።

ወቅታዊው የአገሪቱ ፖለቲካዊ ሁኔታ የማይገመትና እጅግ የተወሳሰበ እንደሆነ ይነገራል፤ በዚህ ላይ አስተያየትዎ ምንድን ነው?

አቶ ወልደሥላሴ ወልደሚካኤል፡ በእኔ እምነት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተገማች [ፕሪዲክተብል] ነው ባይ ነኝ። ተሳስቼ ልሆን ይችላል፤ ግን በነበረኝ የሥራ አጋጣሚ አገሪቷን አውቃታለሁ የሚል እምነት አለኝ።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከ1983 ዓ.ም በኋላ ከስር መሰረቱ ተቀይሯል። የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ጀምረዋል።

የራሳቸውን ሀብት በራሳቸው ማስተዳደር ጀምረዋል። በራሳቸው ፖለቲካዊና ማኅበረ ኢኮኖሚ ጉዳይ መወሰን የጀመሩበት ሁኔታ ነው ያለው። አንዳንድ የፖለቲካ ሊሂቃን ካልሆኑ በስተቀር አብዛኛው ሕዝብ በራሱ ጉዳይ ላይ ብቻ የተጠመደ ነው።

በአሁኑ ወቅት አንዱን ብሔር በሌላኛው ብሔር ላይ ልታነሳሳው አትችልም። ሰለዚህ በዚህ ጉዳይ መሰረታዊ ለውጥ አለ ብዬ ነው እማምነው። ለምሳሌ የኦሮሞ ሕዝብን ጥያቄ የወሰድን እንደሆነ ታሪካዊ በደል ደርሶብናል፣ በብሔርተኛ ልጆቻችን ነው መተዳደር የምንፈልገው፣ ከተፈጥሮ ሀብታችን ተጠቃሚዎች አይደለንም፣ ቋንቋችን በሚፈለገው ደረጃ አላደገም የሚሉ ፍትሀዊ ጥያቄዎች ነው የሚያነሳው እንጂ የትግራይ እና አማራ ጉዳይ ጉዳዩ አይደለም።

የአማራ ህዝብ ጥያቄም የልማት፣ የፍትህና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ናቸው። እንደ አጋጣሚ ከትግራይ ሕዝብ ቀጥሎ አውቀዋለሁኝ የምለው ሕዝብ የአማራን ሕዝብ ነው። የትግራይ ጥያቄም ተመሳሳይ ነው። ከዚህ በኋላ ሕገ መንግሥታዊ ፌደራላዊ ሥርዓቱ ልታጎለብተው ካልሆነ በስተቀር ልትቀይረው አትችልም። ስለዚህ የኢትዮጵያ ፖለቲካ 'ፕሪዲክተብል' ነው ባይ ነኝ።

በቅርቡ ከህወሓት እውቅና አግኝተዋል፤ ይህ ማለት አሁንም የፓርቲው አባል ነዎት ማለትት ነው?

አቶ ወልደሥላሴ ወልደሚካኤል፡ እውቅናው ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለብዙ የቀድሞ ተጋዮች የተሰጠ ነበር። እኔ በህይወት እስካለሁኝ ህወሓት ነኝ። ህወሓት 'ዳይናሚክ' እንዲሆን ነው እምፈልገው። ደግሞ ተራማጅ ድርጅት እንደሆነ ነው የማምነው። ተራማጅ እንዲሆን ያደረገው ግን የሕዝቡ ንቃተ ህሊና ነው። አንዳንድ ሰዎች ህወሓትና የትግራይ ሕዝብ አንድ አይደሉም ሲሉ እሰማለሁኝ እንደ እኔ ግን አንድ ናቸው ባይ ነኝ።

በትግራይ ብዙ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ባሉበት ሁኔታ ሕዝቡና ህወሓት አንድ ናቸው ማለት ተገቢ ነው ይላሉ?

አቶ ወልደሥላሴ ወልደሚካኤል፡ በፖለቲካዊ መነጽር ብቻ ካየነው ህወሓት ህጋዊ የፖለቲካ ድርጅት ነው። ቢሆንም የትግራይ ሕዝብ የህወሓት ፖለቲካዊና ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ስትራቴጂዎችን የእራሱ አድርጓቸዋል። ይህ በጥናትም ሊረጋገጥ የሚቻል ነገር ነው።

የትግራይ ሕዝብን ፖለቲካዊ እምነቱን ብትጠይቀው የህወሓትን ንድፈ ሀሳቦች በይበልጥ ነው የሚያብራራልህ። ታዲያ ይህንን ሀሳብ የሚቃወሙ ሰዎች የሉም ማለት ግን አይደለም።

የትግራይ ሕዝብና ህወሓት አንድ ናቸው የሚለው ሀሳብ ከህወሓት የተሻለ አማራጭ ለትግራይ ህዝብ ይዘናል የሚሉ ድርጅቶችን ማፈን አይሆንም? ሀሳቡስ ለሕዝቡ ጠቃሚ ነው?

አቶ ወልደሥላሴ ወልደሚካኤል፡ በትግራይ ሁሉም ዓይነት ሀሳብና ማኅበራት በነጻ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አምናለሁ። የተለይ የፖለቲካ አማራጭ ያላቸው ሰዎች በነጻነት መደረጃት አለባቸው። አንዳች ተጽዕኖ እና ገደብ ሊደረግባቸው አይገባም። እነዚህ መሰረታዊ የዴሞክራሲ ጭላንጭሎች ስለሆኑ ሊሰመረበት ይገባል።

የእኔ ሀሳብ ግን ህወሓት የምትመራባቸው ሀሳቦች በአብዛኛው ሕዝብ ተቀባይነት አላቸው ብቻ ሳይሆን በሕዝቡ ዘንድ የሰረጹ ናቸው ብዬ ነው እማምነው። ለዚህም ነው ከድሮ ጀምሮ ህወሓት እንቅፋት ሲገጥማት ሕዝቡ ተረባርቦ የሚያድናት።

ይህ ማለት ግን ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶችና ሀሳቦች መምጣት የለባቸውም ማለት አይደለም። እንደውም ህወሓት ተራማጅ ልትሆን የምትችለው ሌሎች አማራጭ ሀሳቦች ሲመጡ ነው ብዬ ነው የማምነው።

በቀጣይነት በመምህርነቱ ይቀጥላሉ ወይስ ወደ ፖለቲካው ይመለሳሉ?

አቶ ወልደሥላሴ ወልደሚካኤል፡ አላውቅም፤ ግን ማስተማር በጣም ይመቸኛል። ከታች ያለውን ፖለቲካ ለመረዳት መንግሥታዊ ኃላፊነት ይዞ ሳይሆን በአካዳሚክ ተቋማት ውስጥ ጥናት እያካሄዱ ሲሆን ይበልጥ ጠቃሚ ነው። ለአሁኑ ትውልድ በአካዲሚክ ተቋማት ሆኜ የራሴን ተሞክሮ እያስተላለፍኩኝ አገሩ ራሱን እንዲያስተዳድር በማድረግ ረገድ የምሰራ ይመስለኛል።