የቶጎ ተቃዋሚዎች መንግሥት ሐሰተኛ የምርጫ ጣቢያዎችን አቋቁሟል ሲሉ ከሰሱ

የቶጎ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር መንግሥት ከትናንት በስቲያ የተካሄደውን ምርጫ ለማሸነፍ ሐሰተኛ የምርጫ ጣቢያዎችን አቋቁሞ ነበር ሲሉ ከሰሱ።

አግቤዮም ኮድጆ የተባሉት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ በፕሬዝደንት ፋኡሬ ግናሲግቤ ላይ ይህን ክስ ቢመሰርቱም እንደ ኤኤፍፒ ዘገባ የፕሬዝደንቱ ጽ/ቤት ክሱን አጣጥሎታል።

ፕሬዝደንት ፋኡሬ ግናሲግቤ መንበረ ስልጣኑን ከአባታቸው በግሪጎሪ አቆጣጠር 2005 ከተቀበሉ ወዲህ ቶጎን እያስተዳደሩ ይገኛሉ።

ከትናንት በስቲያ የተካሄው የፕሬዝደንታዊ ምርጫ ውጤቶች ፕሬዝደንት ግናሲግቤ ለአራተኛ ዙር ምርጫውን ማሸነፋቸውን ያመላክታሉ።

ዛሬ ጠዋት ምርጫ ኮሚሽኑ ፕሬዝደንቱ 72 በመቶ የሚሆነውን ድምጽ ማግኘታቸውንና ዋነኛ ተቃዋሚው አግቤዮም ኮድጆ እስካሁን በተካሄደው ቆጠራ መሰረት ያገኙት ድምጽ 18 በመቶ ብቻ መሆኑን ገልጿል።

ኮድጆ የመንግሥት ባለስልጣናት ግለሰቦች ከአንድ ጊዜ በላይ እንዲመርጡ ፈቅደዋል ሲሉ በተጨማሪ ከሰዋል።

ቅዳሜ ዕለት ድምጽ ተሰጥቶ እንደተጠናቀቀ ለሶስት ሰዓታት ያክልል የተቃዋሚው ኮድጆ መኖሪያ ቤት በወታደሮች ተከቦ እንደነበረ ተዘግቧል።

የቶጎ ደህንነት ሚንስትር ያርክ ዳሜህም ለአሜሪካ ድምጽ እንደተናገሩት፤ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው ኮድጆ መኖሪያ ቤት በወታደሮች እንዲጠበቅ የተደረገው ለራሳቸው ደህንነት ሲባል ነው ብለዋል።

ኮድጆ ለቢቢሲ ሲናገሩ ግን ቤታቸው በወታደር ለምን መክበብ እንዳስፈለገ እንዳልተነገራቸው እና መንግሥት ይህን ያደረገው ምርጫውን ለማጭበርበር በቂ ጊዜ እንዲያገኘው ለማስቻል እንደሆነ አምናለሁ ብለዋል።

ቶጎ 8 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ አላት።

ባለፈው ዓመት የተደረገው ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ፕሬዝደንቱ ለዳግም ምርጫ እንዲወዳደሩ ከማስቻሉም በላይ እስከ አውሮፓውያኑ 2030 ድረስ በስልጣን እንዲቆዩ ያስችላዋል።