ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኬንያዊውን ገርፈዋል የተባሉት ቻይናውያን አሰሪዎች ከሃገር እንዳይባረሩ ፍርድ ቤቱ አዘዘ
ኬንያዊውን ገርፈዋል የተባሉት ቻይናውያን አሰሪዎች ከሃገር እንዲወጡ የተላለፈውን ትዕዛዝ ፍርድ ቤቱ ማገዱ ተዘግቧል።
ከሰሞኑ አንድ ኬንያዊ በቻይናውያን አሰሪዎች በመዲናዋ በናይሮቢ በሚገኝ ሬስቶራንት ውስጥ ሲገረፍ የሚያሳይ ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ተሰራጭቶ ከፍተኛ ቁጣና ንዴት አስከትሏል።
ይህንንም ተከትሎ ፍርድ ቤቱ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ለፖሊስ በሰጠው ትእዛዝ መሰረት አራቱ ቻይናውያን በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የሃገር ውስጥ ሚኒስትር ፍሬድ ማቲያንጊ በአስቸኳይ ከሃገር እንዲባረሩ ትእዛዝ አስተላልፈው ነበር።
ፍርድ ቤቱ ለተጨማሪ 15 ቀናት በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲቆዩም ትእዛዝ ቢያስተላልፍም ክስ አልተመሰረተባቸውም።
አራቱ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉት ከአስር ቀናት በፊት በመዲናዋ ናይሮቢ በተለምዶ ኪለለሽዋ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ቼዝ ው ተብሎ በሚጠራው ሬስቶራንት ውስጥ ነው።
አንደኛው አሰሪ በተለይም በሬስቶራንቱ ተቀጥሮ የሚሰራውን ኬንያዊ አርፍደሃል በሚል በዱላ ደብድቦታል ተብሏል። ይህንን የሚያሳይ ቪዲዮ ብዙዎች ማጋራታቸው ቁጣን በከፍተኛ ሁኔታ እንዳባባሰው ተዘግቧል።