ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቻይና ውስጥ በኮሮና ቫይረስ 97 ሰዎች በአንድ ቀን ሞቱ
በቻይና በትናንትናው ዕለት በኮሮና ቫይረስ ብቻ በአንድ ቀን 97 ሰዎች ሞቱ፤ ይህም ቁጥር እስካሁን በቀን ውስጥ ከተመዘገበው ከፍተኛው ነው ተብሏል።
በኮሮና ቫይረስ የሟቾች ቁጥር 908 የደረሰ ቢሆንም በየቀኑ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ግን ለውጥ አላሳየም እንዲያውም መረጋጋት አሳይቷል እየተባለ ነው።
በአጠቃላይ በቻይና በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ቁጥር 40 ሺ 171 የደረሰ ሲሆን፣ 187 ሺ 518 ግለሰቦች ደግሞ በቅርብ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው ነው።
የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ቫይረሱ ያለበትን ሁኔታ የበለጠ ለመመርመር በቅርቡ የህክምና ባለሙያዎችንና ተመራማሪዎችን የያዘ ቡድን ልኳል።
ከቻይና መንግሥት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው እስካሁን ድረስ በቫይረሱ የተያዙ 3 ሺ 281 ግለሰቦች ህክምና ተደርጎላቸው ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል።
የቻይና አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግና በተጨማሪም ቫይረሱ እንዳይዛመት ተብሎ ስራ እንዲቋረጥ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፤ በዛሬው ዕለት ሚሊዮኖች ወደ ስራ ገበታቸው ተመልሰዋል።
ነገር ግን የስራ ቦታ እንደ ቀድሞው አይሆንም፤ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት፣ እንዲሁም የስራ መግቢያና መውጪያ ሰዓት እንደ አስፈላጊነቱም የሚቀያየር ይሆናል፤ አንዳንድ የስራ አይነቶችም ለተወሰነ ጊዜ ተዘግተው ይቆያሉ።
በኮሮና ቫይረስ የሟቾች ቁጥር በጎርጎሳውያኑ 2003 የተነሳው የሳርስ ወረርሽኝ ከቀጠፈው ህይወት እንደበለጠ ተገልጿል።
የቫይረሱ መነሻ በሆነችው ሁቤ ግዛት የሟቾች ቁጥር 780 እንደደረሰና፤ ቅዳሜ ዕለትም በግዛቷ 81 ሰዎች እንደሞቱ የጤና ባለሙያዎች አስታውቀዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት በቫይረሱ የሚያዙ አዲስ ሰዎች ቁጥር ለውጥ እንደሌለው ከሰሞኑ ገልጿል። በትናንትናው ዕለት ድርጅቱ ዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጪዎችንም ወደ ቻይና ልኳል።
ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በሁቤዋ ግዛት ውሃን ከተማ ሲሆን፤ የአስራ አንድ ሚሊዮን ህዝብ መኖሪያ የሆነችው ውሃን ለሳምንታትም የጉዞ፣ የመውጣትና የመግባት እግድ ተጥሎባታል።
ከሳምንት በፊት ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት የኮሮና ቫይረስን የአለም የጤና ስጋት ነው ብሎታል።
ቫይረሱ ከቻይና ወደ 27 ሃገራት የተዛመተ ቢሆንም ከቻይና ውጭ ያለው የሟቾች ቁጥር ሁለት ነው፤ አንደኛው በሆንግኮንግ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በፊሊፒንስ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ወደ ሆንግ ኮንግ የገባች መርከብ መንገደኞችና ሰራተኞቹ በጥርጣሬ ምክንያት በለይቶ ማቆያ ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆዩ ቢደረግም ከምርመራ በኋላ እንዲወርዱ ተፈቅዶላቸዋል።
ይህቺ መርከብ እንድትለይ የተደረገችው ከዚህ ቀደም በአንዲት የጃፓን መርከብ ላይ ስምንት ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘው በመገኘታቸው ነው።
በጃፓን በመርከቡ ውስጥ ካሉ መንገደኞች መካከል በቫይረሱ የተያዙ መኖራቸው መረጋገጡን ተከትሎ መርከቧ ተለይታ እንድትቆይና መንገደኞችም እንዳይወርዱ ተደርገዋል።
ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ ቫይረሱ ይዛመታል በሚል ፍራቻ ማንኛውም መርከብ ሃገሯ እንዳይገባ እግድ ጥላለች።