ዶናልድ ትራምፕ በህዳሴው ግድብ ላይ በቅርቡ ስምምነት እንደሚደረስ ተናገሩ

ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በታላቁ የህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሁሉንም አገራት በሚጠቅም መልኩ ከስምምነት ላይ እንደሚደርሱ ያላቸውን ተስፋ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገለጹ።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ይህን ያሉት ትናንት አርብ ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጋር በስልክ በተወያዩበት ወቅት መሆኑን የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ መግለጻቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

በስልክ ውይይቱ ላይ ዋሽንግተን ውስጥ ሲካሄድ ስለሰነበተው ውይይት ሁለቱ መሪዎች አንስተው የተወያዩ ሲሆን ትራምፕ "በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ስምምነት ለመድረስ መቃረቡንና ሁሉንም ወገኖች ተጠቃሚ የሚያደርግ" እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።

ከማክሰኞ ጥር 19 ጀምሮ በኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል ዋሽንግተን ውስጥ ሲካሄድ የቆየው ድርድር ከታቀደለት ጊዜ ዘግይቶ ትናንት አርብ ተጠናቋል።

በተከታታይ በተለያዩ ከተሞች ውስጥ ሲደረግ የነበረው ውይይት ላይ የአገራቱ የውጭ ጉዳይና የውሃ ሚኒስትሮች የሕግና የውሃ ጉዳይ ባለሞያዎችን እንዲሁም የአሜሪካ ባለስልጣናትና የዓለም ባንክ ተወካዮች በታዛቢነት ተሳትፈዋል።

ምንም እንኳን በዚህ ድርደር በሁለት ቀናት ውስጥ ከስምምነት ተደርሶ የግድቡ ውሃ መሙላትና የውሃ አለቃቀቅን በተመለከተ መቋጫ ያገኛል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም ሳይሳካ ቀርቷል።

ነገር ግን ለቀናት በቆየው ውይይት ማብቂያ ላይ የአገራቱ ተወካዮች የግድብን የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው በድርቅ ወቅት፣ ለዓመታት የተራዘመ ድርቅ በሚያጋጥምበት ወቅትና ለዓመታት የተራዘመ ደረቅ ወቅት ላይ ስለሚኖረው የውሃ አሞላልን በተመለከተ መሰረታዊ መግባባት ላይ ተደርሷል።

የአገራቱ ሚኒስትሮችም የቴክኒክና የሕግ ቡድኖቻቸው በመሰረታዊነት መግባባት ላይ የተደረሱባቸው ነጥቦችን በማካተት እስከ ፈረንጆቹ የካቲት ወር ማብቂያ ድረስ የመጨረሻ የስምምነት ሰነድ እንዲያዘጋጁ ማዘዛቸውንም በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ አመልክተዋል።

ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳለው ድርድሩ "በግድቡ ብቻ ላይ የተወሰነ መሆኑን፣ እንዲሁም የሀገራችንን ነባርና የወደፊት በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብትን በሙሉ የሚያስከብር ማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት የማይቀየር አቋም ነው" ሲል ገልጿል።

በሦስቱ አገራት መካከል በሕዳሴው ግድብ ላይ እየተደረገ ያለው ድርድር በጥር ወር አጋማሽ ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም በተደራዳሪዎቹ መካከል ከስምምነት ላይ ባለመደረሱ እስከ ፈረንጆቹ የካቲት ወር ማብቂያ ድረስ ለመዝለቅ ተገዷል።

አገራቱ በተለይ ከስምምነት ላይ እንዳይደርሱ ያደረጋቸው ጉዳይ ኢትዮጵያ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ በማውጣት እየገነባቸው ያለው ግድብ የውሃ አሞላል ሂደት ነው። ግብጽ የውሃ ሙሌቱ እስከ 20 ዓመታት በሚደርስ ጊዜ እንዲሆን ስትጠይቅ ኢትዮጵያ ግን ሙሌቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲሆን ትፈልጋለች።

በድርድሩ ላይ ወሳኝ ሚና ያላቸው ኢትዮጵያና ግብጽ ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲሁም የየአገራቱ የሕግና የቴክኒክ አማካሪዎችን ተሳታፊ ሆነዋል።

ከኢትዮጵያ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለን፤ ግብጽ ደግሞ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚህ ሹክሪና የመስኖ ሚኒስትሩ ሞሐመድ አብደል አቲ በዋሽንግተኑ ውይይት ላይ በመሪነት ሲሳተፉ ቆይተዋል።