ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"የኮሮናቫይረስ ክስተት በአሜሪካ የሥራ ዕድልን ሊያሳድግ ይችላል"
ቻይና ውስጥ የተከሰተውና የበርካቶችን ህይወት እየቀጠፈ ያለው የኮሮናቫይረስ ለአሜሪካ ኢኮኖሚ ሲሳይን ይዞ ሊመጣ እንደሚችል የአገሪቱ ንግድ ሚኒስትር ዊልበር ሮስ ተናገሩ።
ሚኒስትሩ ለአንድ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ እንዳሉት "የወረርሽኙ መከሰት የሥራ ዕድሎች ወደ ሰሜን አሜሪካ የሚመለሱበትን ሁኔታ የሚያፋጥነው ይመስለኛል" ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ የንግድ ሚኒስትሩ አስተያየት የትራምፕን አስተዳደር ከሚተቹ ወገኖች ከፍተኛ ተቃውሞን ቀስቅሷል።
የበሽታው በፍጥነት መስፋፋት በቻይና ኢኮኖሚና በዓለም ዕድገት ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል ተብሎ ተሰግቷል።
ሚኒስትሩ ከፎክስ ቢዝነስ ኒውስ በቻይና የተከሰተው ወረርሽኝ በአሜሪካ ኢኮኖሚ ላይ ስጋት ያስከትል እንደሆነ በተጠየቁ ጊዜ "የአሜሪካ ተቋማት የአቅርቦት ሰንሰለታቸውን መለስ ብለው መፈተሽ እንሚያስፈልጋቸውና ክስተቱ ወደ አሜሪካ የሚመለሰውን የሥራ ዕድል በከፍተኛ ደረጃ ሊያሳድገው ይችላል" ብለዋል።
ይህን ንግግር ተከትሎ ከተለያዩ ወገኖች ትችቶች ተሰንዝረዋል ከእነዚህም መካከል የዲሞክራቲክ ፓርቲ የኮንግረስ አባል የሆኑት ዶን ቤየር በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ "ገዳይ ወረርሽኝ በተከሰተበት ጊዜ የንግድ አጋጣሚን መፈለግ" ሲሉ ወቀሳ ሰንዝረዋል።
በኋላ ላይ ግን የመስሪያ ቤታቱ ቃል አቀባይ "ሚኒስትር ሪስ ግልጽ እንዳደረጉት የመጀመሪያው እርምጃ የቫይረሱን ስርጭት መቆጣጠር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የበሽታውን ሰለባዎች መርዳት ነው" ሲል አስተያየት ሰጥቷል።
ቃል አቀባዩ ጨምረውም "በሕዝቧና በቀሪው ዓለም ላይ የተጋረጠን አደጋ በመሸፋፈን ረጅም ታሪክ ካላት አገር ጋር መስራት የሚያስከትለውን ጉዳት ማጤን አስፈላጊ ነው" ሲሉም ቻይናን በነገር ሸንቆጥ አድርገዋል።
ቻይና ውስጥ ከ200 በላይ ሰዎችን የገደለው ይህ በሽታ ከዚህ ቀደም ተከስቶ ከነበረውና ሳርስ በመባል ከሚታወቀው ወረርሽኝ በከፋ ሁኔታ በዓለም ምጣኔ ሐብት ላይ ከፍ ያለ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል ባለሙያዎች ተናግረዋል።
ከ18 ዓመት በፊት ተከስቶ የነበረው የሳርስ በሽታ ከ8 ሺህ በላይ ሰዎችን ይዞ የነበረ ሲሆን ከ700 በላዩን ለሞት ዳርጓል። በበሽታው ሳቢያ ዓለም አቀፉ ኢኮኖሚ ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ ጉዳት ደርሶበታል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የቻይና ባለስልጣናት በመላው አገሪቱ የእንቅስቃሴ ገደብ በመጣላቸው ግዙፎቹን የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችና መኪና አምራቾች እንዲሁም የንግድ ተቋማት ለጊዜው ሥራ አቁመዋል።