ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኃይለኛ ንፋስ ትራምፕ በሜክሲኮ ድንበር እያስገነቡ ያሉትን አጥር አፈረሰ
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ እና ሜክሲኮ ድንበር ላይ እያስገነቡ ያሉት አጥር በኃይለኛ ንፋስ መፍረሱን የአሜሪካ ባለስልጣናት አስታወቁ።
በሜክሲኮዋ ካሌክሲኮ እና በአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ከተሞች መካከል እየተገነባ የነበረው የአጥሩ አካል ረቡዕ ጠዋት አካባቢ በኃይለኛ ንፋስ መውደቁ ተነግሯል።
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ የሚሻገሩ ስደተኞችን ለማስቆም በማሰብ በሁለቱ አገራት መካከል አጨቃጫቂ የሆነውን ረዥም የብረት አጥር እየስገነቡ እንደሆነ ይታወቃለ።
ከፍታው 9 ሜትር የሚረዝመውን የብረት አጥር ለማቆም የተገነባው ኮንክሪት አለመድረቁ ለአጥሩ በንፋስ መውደቅ እንደምክንያት ተጠቅሷል።
የአሜሪካ ብሔራዊ ሜትሪዮሎጂ አገልግሎት እንዳስታወቀው በወቅቱ የነበረው የንፋስ ፍጥነት በሰዓት 48 ኪ.ሜትር ይደርስ ነበር።
ትራምፕ ስድተኞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ይረዳኛል ያሉት የአጥር ግንባታ 3145 ኪሎ ሜትር በላይ ይረዝማል።
ከትናንት በስቲያ ፕሬዝደንት ትራምፕ በኒው ጀርሲ ባደረጉት የምርጫ ቅስቀሳ ላይ እያስገነቡት ያሉት የአጥር ግንባታ "ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት" ግንባታው እየተካሄድ እንደሆነ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረው ነበር።
ትራምፕ ይህን ባሉ በአንድ ቀን ልዩነት የአጥሩ ክፍል በንፋስ ወድቋል።
የአሜሪካ ድንበር ጥበቃ ለኤልኤ ታይምስ እንደተናገሩት አጥሩ በንፋስ መውደቁን ተከትሎ በሰው እና በንብረት ላይ ያደረሰው ጉዳት የለም።
በንፋሱ የወደቀ እና የተወላገደ የአጥሩን ክፍል ለማቃናት ጥረት የሚያደርጉ ክሬኖች ታይተዋል።
ትራምፕ ለፕሬዝደንትነት ሲወዳደሩ ካነሷቸው ሀሳቦች መካከል በሜክሲኮ እና በአሜሪካ መካከል የግንብ አጥር መገንባት አንዱና አጨቃጫቂው ሃሳባቸው ነበር። ትራምፕ በወቅቱ ለአጥሩ ግንባታ ወጪውን የምትሸፍነው ሜክሲኮ ነች ሲሉም መደመጣቸው ይታወሳል።
ሜክሲኮ ግን ለአጥሩ ግንባታ ስባሪ ሳንቲም እንደማታወጣ ካስታወቀች በኋላ፤ ትራምፕ ከፔንታጎን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ለአጥሩ ወጪ መሸፈኛ ፈንድ አስባስበዋል።
ፔንታጎን በአሜሪካ እና በሜክሲኮ ድንበር ላይ ለሚገነባው አጥር 3.4 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል።