ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአዲሱ ቫይረስ የሟቾች ቁጥር አሻቀበ
ከቻይና የዓሣ ጉሊት እንደተነሳ የሚገመተው ኮሮና ቫይረስ እስከ ትናንት የሟቾች ቁጥር 81 የነበረ ቢሆን በአጭር ሰዓታት ውስጥ 106 መድረሱ ድንጋጤን ፈጥሯል።
እስከዛሬ የተረጋገጡ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር 4 ሺህ 515 ደርሷል። ይህ ቁጥር ከቀናት በፊት 2835 ነበር።
የተያዦች ቁጥር ማሻቀቡን ተከትሎ ቻይና የጉዞ እቀባዋን አጠናክራለች።
የቫይረሱ መነሻ ናት የምትባለው የዉሃን ከተማ በሁቤት ክፍለ ግዛት የምትገኝ ትልቅ ከተማ ስትሆን 11 ሚሊዮን ሕዝብ ይኖርባታል። ወደ 700ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ተማሪዎች ናቸው። ከተማዋ ለጊዜው በጉዞ እቀባ ላይ ናት።
ኮሮናቫይረስ የመተንፈሻ አካላትን ዕለታዊ ተግባራቸውን የሚያስተጓጉል ቫይረስ ሲሆን እስከዛሬም ፈውስም ሆነ ክትባት አልተገኘለትም።
ብዙዎቹ እየሞቱ ያሉት ግን ቀድሞመው መተንፈሻ አካላት ጋር በተያያዘ ችግር ያለባቸው እና በእድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች መሆናቸውን የሕክምና ሰዎች መታዘብ ችለዋል።
ቻይና ምን እያደረገች ነው?
የቻይና አዲስ ዓመት ላይ የተከሰተው ይህ ቫይረስ ለቁጥጥር እጅግ አስቸጋሪ ሆኗል። ምክንያቱ ደግሞ ይህ የቻይናዊያን አዲስ ዓመት በመቶ ሚሊዮኖች የሚገመተው ቻይናዊ ከከተማ ከተማ፣ ከግዛት ግዛት፣ ከአገር አገር የሚጓጓዝበት ሁነኛው ወቅት በመሆኑ ነው።
የቻይና መንግሥት በዓሉን ከግምት ውስጥ በማስገባት አብዛኛዎቹን የበዓል መርሃ ግብሮች ሰርዟ። ዜጎቿ ባሉበት እንዲቆዩ በማሰብም ክብረ በዓሉን በሦስት ቀናት ገፍታለች። ይህም በመሆኑ አርብ ያበቃ የነበረው በዓል እስከ እሑድ ይዘልቃል።
ቤይጂንግ ከሁቤይ ክፍለ ግዛት የሚነሱ አውቶቡሶችን ያስቆመች ሲሆን ቤይጂንግም ሆነ ሻንጋይ ከሁቤት ወደ ሌሎች ከተሞች የሚገቡ ሰዎች በትንሹ ለ14 ቀናት ክትትል እያደረግችላቸው ነው።
ከ106 ቻይናዊያን ሟቾች 100 የሚሆኑት ከዚሁ የሁቤይ ክፍለ ግዛት የመጡ ናቸው።
በዓለማቀፍ ደረጃ ያሉ እውነታዎች
አሜሪካ ዜጎቼ "እባካችሁ ወደ ቻይና መሄድ ይቅርባችሁ" የሚል ምክር ሰጥታለች። በተለይ ደግሞ ወደ ሁቤይ ክፍለ ግዛት "በፍጹም እግራችሁን እንዳታነሱ" ብላለች።
በሚቀጥሉት ቀናትም ዜጎቿንና የኤምባሲ ሰዎቿን ከዉሃን ከተማ ለማስወጣት አቅዳለች።
ሌሎችም የአውሮፓ አገሮች ተመሳሳይ ተግባር እየፈጸሙ ይገኛሉ።
ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የሚመሩት የዓለምአቀፉ የጤና ድርጅት ባወጣው መረጃ በትንሹ 47 የቫይረሱ ተጠቂዎች የሚገኙት ከቻይና ውጭ ነው።
በዚህም መሠረት 8ቱ ከታይላንድ ሲሆኑ፣ አሜሪካ ሲንጋፖርና ታይዋን እያንዳንዳቸው 5 ታማሚዎች ተመዝግበውባቸዋል።
ማሌዢያ፣ ደቡብ ኮሪያና ጃፓን እያንዳንዳቸው 4፣ ፈረንሳይ 3፣ ቬትናም 2 ዜጎቻቸው ታመውባቸዋል።
ኔፓል፣ ካናዳ፣ ካምቦዲያ፣ ስሪላንካና ጀርመን እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ዜጋ በቫይረሱ መያዙን አረጋግጠዋል።
እስካሁን ከቻይና ውጭ በቫይረሱ ተይዞ የሞተ ግን አልተመዘገበም።