በቻድ ሐይቅ ላይ በተፈፀመ ጥቃት በርካታ አሳ አስጋሪዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Google map
ካሜሩንንና ቻድን በሚያዋስነው የቻድ ሐይቅ ላይ በተፈፀመ ጥቃት ቢያንስ 50 አሳ አስጋሪዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ።
ጥቃት ፈፃሚዎቹ የቦኮሃራም ታጣቂዎች ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ተገምቷል።
ነጋዴዎች መስለው እንደገቡ የተነገረው ታጣቂዎቹ፤ በአሳ አስጋሪዎቹ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን የአካባቢው ከንቲባ አሊ ራማት ከጥቃቱ የተረፈውን ግለሰብ ጠቅሰው ተናግረዋል።
ጥቃቱ ታህሳስ 12 የደረሰ ቢሆንም ድርጊቱ የተፈፀመበት አካባቢ ከከተማ ወጣ ያለ በመሆኑ መረጃ መሰማት የተጀመረው ግን በቅርቡ ነው።
በናይጄሪያ በአውሮፓዊያኑ 2009 የተመሠረተው ቦኮሃራም፤ ከምስረታው ጀምሮ እንቅስቃሴውን በጎረቤት አገር ቻድ፣ ካሜሩንና ኒጀር አስፋፍቷል።
በካሜሩን ሰሜናዊ ግዛት፤ የዳራክ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ራማት ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ በጥቃቱ ከሞቱት መካከል 20 ካሜሮናዊያን ይገኙበታል። ሌሎች ማንነታቸው ያልተለዩ እና ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መኖራቸውንም ከንቲባው አክለዋል።
ይሁን እንጅ ሟቾቹ የተለያየ ዜግነት እንዳላቸው የታመነ ሲሆን፤ አንዳንዶቹ በሐይቁ ላይ አሳ በማስገር ሥራ ላይ ተሰማርተው ነበር።
በታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ ጥቃት ወደ ደረሰበት አካባቢ ለፍለጋ የተሰማሩ ከአካባቢው የተወጣጡ የማህበረሰብ አባላት፤ የሟቾቹ አስክሬን በውሃ ላይ ተንሳፎ ማግኘታቸውን በሥፍራው የሚገኘው የቢቢሲ ወኪል ዘግቧል።
የአካባቢው አስተዳዳሪ ሚዲጂያዋ ባካርይ፤ ጥቃቱ መፈፀሙን አረጋግጠዋል።
ከንቲባ ራማት፤ የቻድ ወታደሮች በአካባቢው መዘዋወር ካቆሙ አንስቶ አካባቢው የቦኮሃራም ጥቃት ኢላማ ሆኖ ነበር።
ከንቲባው አክለውም፤ በቻድ ሐይቅ ተፋሰስ አካባቢ ካሉ አምስት አገራት ወታደራዊ ኃይል የተወጣጣው ጥምር ኃይል በአካባቢው ጥበቃ ለማድረግ በቂ ትጥቅ አልነበረውም ብለዋል።












