አሜሪካ ጣዕም ያላቸው የኤሌክትሮኒክ ትምባሆ ምርቶችን ከገበያ አገደች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዩናይትድ ስቴትስ፤ ታዳጊዎችን ከሱስ ለመታደግ በሚል በተለያየ ቃና የሚመረት ኤሌክትሮኒክ ትምባሆ ከገበያ ውጭ እንዲሆኑ አዘዘች።
ጁል የተባለ ኩባንያ የሚያመርታቸው ሚንት እና የተለያዩ ፍራፍሬዎች ቃና ያላቸው ኤሌክትሮኒክ የትምባሆ ምርቶች ናቸው ከመላው አሜሪካ ገበያ ውጭ እንዲሆኑ የታዘዘው።
ነገር ግን የትምባሆ ሽታ ያላቸው እና ሌሎች ኤሌክትሮኒክ ትምባሆዎች አሁንም ገበያ ላይ ናቸው።
የአሜሪካ አንዳንድ ክፍለ-ግዛቶች አስቀድመው ዕገዳ ጥለው ነበር።
ደቡብ ኮሪያ፣ ሕንድ እና ብራዚል ቃና ያላቸው የኤለክትሮኒክ ትምባሆ ምርቶች ከገበያ ውጭ እንዲሆኑ ካዘዙ አገራት መካከል ናቸው። ቻይና ደግሞ ምርቱ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ታደርጋለች።
ቃና ያላቸው ኤሌክትሮኒክ ሲጋራዎችን መጠቀም [ቬፒንግ] ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወጣቶች ዘንድ እየተለመደ የመጣ ክስተት ነው።
ይህ ያሳሰበው የትራምፕ አስተዳደር ሲጋራዎቹ ከገበያ ውጭ እንዲሆኑ ያዘዘው በኤሌክትሮኒክ ሲጋራዎች ጉዳት የሚደርስባቸው ታዳጊዎች ቁጥር በመጨመሩ ነው።
የአሜሪካ የጤና ቢሮ ሰዎች በኤሌክትሮኒክ ሲጋራዎች ምክንያት 56 ሰዎች ሲሞቱ 2500 ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው ሆስፒታል ገብተዋል ይላሉ።
የችግሩን መንስዔ እየመረመሩ ያሉ ግለሰቦች ኤሌክትሮኒክ ትምባሆ ውስጥ ማሪዋና ጭምሮ መጠቀም ጉዳት እያስከተለ እንደሆነ ይገምታሉ።
ጁል የተሰኘው በአሜሪካ ትልቁ የኤሌክትሮኒክ ትምባሆ አምራች ድርጅት ቃና ያላቸው ሲጋራዎች ማምቱን አቁሟል። ሌሎች ድርጅቶችም ምርቱን ከገበያ ውጭ ለማድረግ የ30 ቀንድ ዕድሜ ተሰጥቷቸዋል።
የትምባሆና ሜንቶል የተባለው ቃና ያላቸው ሲጋራዎች ለጊዜው ያልታገዱ ሲሆን ዘግየት ብሎ መታገዳቸው የሚቀር አይደለም እየተባለው ነው።












