ማጤስ እንደሳንባችን ሁሉ ዓይናችንንም ይጎዳል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዩናይትድ ኪንግደም ዜጎች በማጨስ ብቻ እይታቸውን አደጋ ላይ እየጣሉ መሆኑን የሕክምና ባለሙያዎች ተናገሩ።
የዓይን ሕክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት ከአምስት ሰዎች መካከል አንዱ ብቻ ነው ትምባሆ ማጨስ የዓይን ብርሀንን እንደሚያሳጣ እውቀት ያለው።
ከማያጨሱ ሰዎች ይልቅ ይላሉ ባለሙያዎቹ፤ የሚያጨሱ ሰዎች በሁለት እጥፍ የዓይን ብርሃናቸውን የማጣት እድላቸው ከፍ ያለ ነው።
የዓይን ህክምና ባለሙያ የሆኑት አይሻ ፋዝላኒ እንደሚሉት "ሰዎች ማጨስና ካንሰር ያላቸውን ግንኙነት በሚገባ ያውቃሉ፤ ነገር ግን ማጨስ የአይን ብርሃን ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት አይረዱትም።"
ትምባሆ ማጨስ የዓይን ብርሃንን በከፍተኛ ሁኔታ ለጉዳት ይዳርጋል ይላሉ ባለሙያዎቹ።
የሲጋራ ጭስ አይንን የሚያቃጥልና እይታን የሚጎዳ መራዥ ኬሚካል በውስጡ ይዟል።
ባለሙያዎቹ አክለውም ማጨስ ከስኳር ጋር ተያይዞ የሚመጣ የዓይን ህመምን በማባባስ የደም ስሮችን ይጎዳል ይላሉ።
አጫሾች ከእድሜ ጋር ተያይዞ የሚመጡ የእይታ መቀነሶች ከማያጨሱት ይልቅ በሶስት እጥፍ ተባብሶ የሚታይባቸው ሲሆን ጥቃቅን ነገሮች ለመለየት ያላቸው ችሎታም ይደክማል።
ዶ/ር አይሻ "ማጨስ ከእድሜ ጋር ተያይዞ የሚመጣን የእይታ መድከም በማባባስ ለዓይነስውርነት የማጋለጥ እድሉ ከፍተኛ በመሆኑ አጫሾች ማጤስ ለማቆም መወሰን ይኖርባቸዋል" ሲሉ ምክራቸውን ይለግሳሉ።
ከማያጨሱ ሰዎች ይልቅ የሚያጨሱ ሰዎች በድንገተኛ የዓይን ብርሃን መጥፋት የመጋለጣቸው እድል 16 እጥፍ የላቀ ነው የሚሉት ባለሙያዎች፤ ይህ የሚሆነው ወደ ዓይን የሚሄደው የደም ፍሰት በድንገት ሲቋረጥ መሆኑን ይናገራሉ።
ባለሙያዎቹ አክለውም ማጨስን ማቆም አልያም ማቋረጥ የአይን ብርሃናን ከአደጋ ለመከላከል ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ጠቅሰው በየጊዜው ምርመራ ማድረግንም ይመክራሉ።
















