ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአንድ የቤተሰብ አባላት የሆኑ ሶስት ሰዎች ሰጥመው ሞቱ
የአንድ የቤተሰብ አባላት የሆኑ ሶስት ሰዎች ስፔን ውስጥ በሚገኘው ኮስታ ዴል ሶል ሪዞርት ውስጥ ሰጥመው መሞታቸው ተገልጿል።
በፈረንጆቹ ገና ዋዜማ ዕለት የመዋኛ ገንዳ ውስጥ የተገኙት የቤተሰብ አባላት ሰዎች ደርሰው ሲያወጧቸው ምንም አይነት እንቅስቃሴ አልነበራቸውም ብሏል የድርጅቱ አስተዳደር።
አንዳንድ ዘገባዎች ይዘውት በወጡት መረጃ መሰረት አንዲት የዘጠኝ ዓመት ታዳጊ ወደ ውሃው ገብታ ስትቸገር የተመለከቱት ወንድሟና አባቷ ወደ ውሀው ውስጥ ዘልለው ገብተዋል።
የእንግሊዝ ውጭ ጉዳይ ቢሮ በበኩሉ ስፔን ውስጥ የምትገኝና አደጋ ያጋጠማት አንዲት ዜጋ እየረዳ መሆኑን ገልጿል። ከሟቾቹ መካከል አባትና ሴት ልጅ እንግሊዛውያን ሲሆኑ ወንዱ ልጅ ግን አሜሪካዊ ነው ተብሏል።
የታዋቂው ሪዞርት አስተዳደር በበኩሉ አደጋው ከተከሰተ በኋላ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በቦታው በፍጥነት በመድረስ የመጀመሪያ እርዳታ ለመስጠት ሙከራ አድርገዋል።
"የኮስታ ዴል ሶል ሪዞርት ሰራተኞችና አመራር በአደጋው ለተጎዱ ቤተሰቦችና ወዳጆች በሙሉ ከልብ የመነጨ መጽናናትን ይመኛል'' ብሏል ድርጅቱ።
አክሎም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበርም የምርመራ ስራውን እያከናወንን ነው ብሏል።