የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጁ በዋጋ የሚያንራቸው ምርቶች

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታህሳስ 7 2012 ዓ.ም ባካሄደው ስድስተኛ መደበኛ ስበሰባው የተለያዩ ረቂቅ አዋጆች ላይ ተወያይቶ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።

ከእነዚህ ረቂቅ አዋጆች መካከል ተሻሽሎ የቀረበው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ይገኝበታል።

በሥራ ላይ የሚገኘው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ያሉበትን ጉድለቶች መቅረፍ ያስችላል ተብሎ የቀረበው ይህ ረቂቅ አዋጅ፤ በሃገር ውስጥ በሚመረቱና ከውጪ በሚገቡ የተመረጡ ምርቶች ላይ ተጨማሪ ታክስ ጥሏል።

ረቂቅ አዋጁ የኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣልባቸው የለያቸው የምርቶች አይነት የሚከተሉት አይነት ናቸው።

  • የቅንጦት የሚባሉ ምርቶች
  • የማህብረሰቡን ጤና ሊጎዱ እና ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ የሚባሉ ምርቶች እንዲሁም
  • መሠረታዊ በመሆናቸው ምክንያት የገበያ ተፈላጊነታቸው የማይቀንስ ዕቃዎች እና አገልግሎቶች ላይ ነው።

መሠረታዊ በመሆናቸው ምክንያት የገበያ ተፈላጊነታቸው አይቀንሱም የተባሉት የምርቶች አይነት፤ እቃዎቹ ኤክሳይዝ ታክስ ስለተጣለባቸው በተጠቃሚዎች ላይ ብዙም የዋጋ ልዩነት የማያመጡ፤ ነገር ግን ለመንግስት ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ ስለመሆናቸው ተነግሯል።

በረቂቅ አዋጁ ላይ የኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣልባቸው ከተለዩ ምርቶች መካከል የሚከተሉት ተጠቃሽ ናቸው።

ኤክሳይዝ ታክስ ለመንግሥት ከፍተኛ ገቢ ከማስገኘቱ በተጨማሪ፤ ከውጪ የሚገቡ እቃዎች ሃገር ውስጥ የተመረቱትን ከገበያ ውጭ እንዳያደርጓቸው ታስቦ ይጣልባቸዋል። ይህም የሃገር ውስጥ አምራቾችን እንደሚያበረታታ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ኤክሳይዝ ታክስ በአምራቹ ወይም አስመጪው ይከፈላል። ምርቶች የተመረቱት በሃገር ውስጥ ከሆነ፤ ከተመረቱበት ወር ቀጥሎ ባሉት 30 ቀናት ውስጥ እንዲሁም ምርቶቹ ከውጪ የሚገቡ ከሆነ አስመጪው ግለሰብ ወይም ድርጅቱ ከጉምሩክ ክልል በሚያወጣበት ጊዜ ታክሱ ይከፈላል፡፡

ይህ ረቂቅ አዋጅ የሚጸድቅ ከሆነ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ 307/1995 ተሽሮ በዚህ አዋጅ ይተካል።

በተጨማሪም ከዚህ አዋጅ ጋር የሚቃረን ማንኛውም ሕግ፣ መመሪያ ወይም አሠራር ይህንን አዋጅ በሚመለከት ተፈፃሚነት አይኖረውም።