ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለየት ያለው የታይላንድ የማሳጅ ጥበብ በባህላዊ ቅርስነት ተመዘገበ
ጠንከር ያለው የታይላንድ ባህላዊ ጀርባን የማሸት ዘዴ ከፍተኛ ቦታ በሚሰጠው የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ዝርዝር ውስጥ ተመዘገበ።
'ኑዋድ ታይ' የተባለው ይህ ባህላዊ መታሻ ጥበብ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፉ ባህሎችና የተለያዩ ተግባራት በሚመዘገብበት የሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርሶች መካከል አንዱ ሆኗል።
በዚህም ለቀጣይ ትውልድ ተጠብቀው መቆየት ካለባቸው ባህላዊ ተግባራት መካከል አንዱ ተደርጎ እንዲመዘገብ ሆኗል።
እነዚህ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ዝርዝር ለተለያዩ ግንባታዎችና ቦታዎች ዕውቅና ከሚሰጠው ከዓለም የቅርሶች ዝርዝር የተለየ ነው።
ባህላዊ ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ እስካሁን በሦስት ዘርፎች የተከፈሉና ከ127 አገራት የተወጣጡ 550 ቅርሶች ተመዝግበዋል። በዝርዝሩ ውስጥ በየዓመቱ የተለያዩ ቅርሶች ተመዝግበው ይካተታሉ።
ይህ የታይላንድ የማሸት ጥበብ ከሌሎች የተለየ ሲሆን በተለያዩ የሰውነት አቅጣጫዎች በኩል በመሆን የተለያዩ ተከታታይ እንቅስቃሴዎችን ያካተተ መሆኑም ተነግሯል።
የ'ናኡድ ታይ' ባለሙያዎች የማሸቱን ተግባር ሲያከናውኑ ምንም አይነት ቅባትም ሆነ ዘይት የማይጠቀሙ ሲሆን እጃቸውን ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ጊዜም ክንዳቸውንና ጉልበታቸውንም ይጠቀማሉ።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የባህልና የሳይንስ ተቋም (ዩኔስኮ) እንዳለው ይህ ተግባር ከጥንት ጀምሮ በታይላንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የነበረ ሲሆን በግብርና ሥራ ላይ የጡንቻ ህመም ሲገጥማቸው በየመንደሩ ያሉ የማሸት ሙያ ያላቸው ሰዎች ጋር በመሄድ ይታሹ ነበር።
በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች መዝገብ ውስጥ ከሚካተቱት መካከል መዝሙርና ዘፈኖችን ጨምሮ የተነገሩ ታሪኮች ሲኖሩበት እነዚህም ለቀጣይ ትውልድ ተጠብቀው ቢተላለፉ ጠቃሚ ይሆናሉ የተባሉትን ነው።