የዓለማችን ውቅያኖሶች ኦክስጂን እያጠራቸው ነው

ሻርክ

የፎቶው ባለመብት, IUCN

የአየር ጸባይ ለውጥና የውሀ አካላት በተለያዩ ነገሮች መበከል ምክንያት በውቅያኖሶች ውስጥ የሚገኘው ኦክስጂን መጠን መቀነስ በርካታ የአሳ ዝርያዎችን ሊያጠፋ እንደሚችል ተገለጸ።

በዚሁ ዙሪያ ጥናቱ የሰሩ ተመራማሪዎች እንደሚሉት 700 ከሚሆኑ የተለያዩ የውቅያኖስ ክፍሎች ላይ በተደረገ ጥናት ውቅያኖሶቹ በእጅጉ ኦክስጂን እያጠራቸው ሲሆን በአውሮፓውያኑ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ከፍተኛ መቀነስ ታይቷል።

በዚህም ምክንያት እንደ ቱና፣ ማርሊን እና ሻርክ ያሉ የአሳ ዝርያዎች የመጥፋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል።

ወደ ውሃ አካላት የሚለቀቁ ኬሚካሎች ደግሞ ለኦክስጂን መጠን መቀነስ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው። በተለያዩ ፋብሪካዎችና ትላልቅ እርሻዎች የሚለቀቁት እንደ ናይትሮጂን እና ፎስፈረስ ያሉ ኬሚካሎች በተለይ ደግሞ በዳርቻዎች አካባቢ ለሚገኙ አሳዎች መሞት ምክንያት ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ የአየር ጸባይ ለውጥም ከፍተኛ ተጽዕኖ እየፈጠረ ነው።

ከምን ጊዜውም በበለጠ ከፍተኛ መጠን ያለው ካርቦን ዳይኦክሳይ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቅ ሲሆን ይህ ደግሞ ከፍተኛ ሙቀት እንዲፈጠር ያደርጋል። ውቅያኖሶችና ሌሎች ትልልቅ የውሀ አካላት ሙቀቱን ሰብስበው ይይዙታል። ሙቅ ውሀ ደግሞ በውስጡ ብዙ ኦክስጂን መያዝ አይችልም።

ተመራማሪዎቹ እንደገመቱት አ.አ.አ. ከ 1960 እስከ 2010 ባሉት ዓመታት በውቅያኖሶች የሚገኘው የኦክስጂን መጠን በአማካይ 2 በመቶ ቀንሷል።

ምናልባት ይህ ቁጥር ትንሽ ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን ቁጥሩ የዓለማችን አማካይ ስለሆነ ነው እንጂ በአንዳንድ ሞቃታማ አካባቢዎች እስከ 40 በመቶ ድረስ ቀንሷል።

ኦክስጂን

የፎቶው ባለመብት, IUCN

እንደ ቱና፣ ማርሊን እና ሻርክ ያሉ የአሳ ዝርያዎች በተለየ ሁኔታ ከፍተኛ የኦክስጂን መጠን በውሃ ውስጥ ይፈልጋሉ። ይህ ሁኔታ ለነዚህ የዓለማችን ህዝብ በብዛት ለሚመገባቸው አሳዎች መጥፎ ዜና ነው።

ትልልቅ አሳዎች በውሀ ውስጥ ለመንቀሳቀስ ከፍተኛ ሃይል የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ያለ ኦክስጂን ደግሞ ይህ የማይታሰብ ነው። ታዲያ እነዚህ አሳዎች ኦክስጂን ፍለጋ ትልቅ ወደሚባለው የውቂያኖስ ክፍል መሸሽን እየመረጡ ነው።

ሀገራት በዚሁ ውቅያኖሶችን የመበከል ስራቸው የሚቀጥሉ ከሆነ እ.አ.አ. በ 2100 የምንላቸውን አሳዎች አናገኛቸውም ማለት ነው። ይህ ደግሞ አንድ የምግብ ምንጭ ከሰው ልጆች ተነጠቀ ማለት ነው።

የውቅያኖሶች አሰራር አሁንም የሰው ልጅ ሙሉ በሙሉ ተመራምሮ ያልደረሰበት እንደመሆኑ እንዲህ አይነት እክሎች ምን አይነት አደጋ ይዘው ሊመጡ እንደሚችሉ መገመት እጅግ ከባድ ነው።