የኮሌስትሮል መጠናችን ማወቅ ያለብን መቼ ነው?

ማንኛውም ሰው የኮሌስትሮል መጠኑን በሃያዎቹ አጋማሽ እድሜ ላይ ማወቅ እንዳለበት ተመራማሪዎች ገለጹ።

ተመራማሪዎቹ እንደገለጹት የኮሌስትሮል መጠንን ቀድሞ ማወቅ በህይወታችን ሊያጋጥሙን የሚችሉ የልብ በሽታ እና ስትሮክ የመከሰት ዕድላቸው ምን ያክል እንደሆነ ለማስላት ቸእድልን ያሰፋል።

በዘርፉ ብዙ ጥናቶች የሰሩት ባለሙያዎች ሰዎች ቀድመው የኮሌስትሮል መጠናቸውን ማወቃቸውና ህክምና መጀመራቸው በምድር ላይ የሚኖራቸውን ቆይታ የመወሰን አቅም ሊኖርው ይችላል ብለዋል።

ኮሌስትሮል በጮማ የተሞላ ንጥረ ነገር ሲሆን በአንዳንድ ምግቦች ውስጥ የሚገኝና በጉበታችን ውስጥም የሚመረት ነው።

ኮሌስትሮል በትክክለኛው መጠን ሲሆን እንደ 'ኦስትሮጂን' እና 'ቴስተስትሮን' ያሉ ሆርሞኖችን ለማምረት እንዲሁም ቫይታሚን ዲ እና ሌሎች ውህዶችን ለመቆጣጠር ይረዳል።

ሁለት የኮሌስትሮል አይነቶች አሉ፡

  • ከፍተኛ የሊፖፕሮቲን ክምችት ያለው ኮሌስትሮል- ጠቃሚ የሚባለውና ለሰውነታችን ጤናማ ሥራ የሚሰራው
  • ዝቅተኛ የሊፖፕሮቲን ክምችት ያለው ኮሌስትሮል- ጎጂ የሚባለውና የደም ስሮችን የሚደፍን ነው

በ 19 ሀገራት በሚገኙ 400 ሺ ሰዎችን አካትቶ የተሰራው ጥናት መጥፎ በሚባለው የኮሌስትሮል መጠን እና የተለያዩ የልብ በሽታዎች መካከል ያለውን ግንኙነትና እድሜያችን ከ 40 ሲያልፍ ሊከሰቱ ስለሚችሉ ተያያዥ ችግሮች መረጃ ሰብስቧል።

ተመራማሪዎቹ እድሜያቸው 35 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች በመውሰድ፤ በጾታቸው፣ መጥፎ የኮሌስትሮል መጠን ክምችት፣ እድሜ፣ ሲጃራ እና መጠጥ ያሉ መጥፎ ልማዶች፣ ስኳር፣ ቁመት፣ ክብደት እና በደም ግፊታቸው መሰረት ለልብ በሽታ የመጋለጥ ዕድላቸውን ለመተንበይ ሞክረዋል።

ከሀምቡርግ የልብ ማዕከል የመጡትና በጥናቱ ተሳታፊ የሆኑት ፕሮፌሰር ስቴፋን ብላንክንበርግ እንደሚሉት የኮሌስትሮል መቆጣጠሪያ መድሃኒቶችን የሚወስዱ ሰዎች በእድሜያቸው ቀጣዮቹ 10 ዓመታት ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ የልብ በሽታዎችን በደንብ መከላከል ይችላሉ'' ብለዋል።

በእንግሊዝ የሚገኙ እስከ 8 ሚሊየን የሚደርሱ ሰዎች 'ስታቲንስ' የተባለውን በደም ውስጥ መጥፎ የኮሌስትሮል መጠን መቀነሻ መድሃኒት ይወስዳሉ።

ምንም እንኳን ውጤታማነቱ ላይ ብዙ ጥያቄዎች ቢነሱም መድሀኒቱን ለተከታታይ አምስት ዓመቱ ከወሰዱ 50 ሰዎች መካከል አንዱ ለልብ ድካም ወይም ስትሮክ የመጋለጥ ዕድሉን በእጅጉ ይቀንሳል።

በአካላዊ እንቅስቃሴ የተሞላና ጤናማ አመጋጋብ ደግሞ የኮሌስትሮል መጠንን ለመቆጣጠር ሁነኛ መንገዶች ናቸው።

ፕሮፌሰር ስቴፋን ብላንክንበርግ በበኩላቸው በተለይ እድሜያቸው ያልገፉ ሰዎች በጊዜ የኮሌስትሮል መጠናቸውን አውቀው የራሳቸውን ውሳኔ ቢያደርጉ ተመራጭ ነው ብለዋል።

''መድሃኒቱን መውሰድ አንድ አማራጭ ሲሆን አካላዊ እንቅስቃሴና ጤናማ አመጋጋብ ግን ሁሉም ሰው ከግምት ውስጥ ሊያስገባቸው የሚገቡ ናቸው።''