ህወሓት ከኢህአዴግ ለመፋታት ቆርጧል?

ሐሙስ በተካሄደውና ግንባሩ የመዋሃድን ሃሳብ በሙሉ ድምፅ ባፀደቀበት በኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ እንደማይገኝ ቀድሞ ያስታወቀው ህወሓት በተግባርም ጉባኤውን ሳይሳተፍ ቀርቷል።

ባለፉት ጊዜያት መንግሥት/ኢህአዴግ የሚያስተላልፋቸውን ውሳኔዎች በተለያየ ምክንያት እንደማይቀበል በመግለጫዎች ሲያስታውቅ ለቆየው ህወሓት በኢህአዴግ የምክር ቤት ስብሰባ ላይ አለመገኘት በያዘው የተቃውሞ ጉዞው ጉልህ ሊባል የሚችል ተጨባጭ እርምጃ እንደሆነ ይታመናል።

ህወሓት በዚህ አቋሙ ፀንቶ ከኢህአዴግ ጋር ይለያያል? የኢህአዴግና የህወሓት ፍቺ እውን የሚሆን ከሆነ ፖለቲካዊና አገራዊ አንድምታው ምን ሊሆን ይችላል? የሚሉ በርካታ ጥያቄዎች የብዙዎች መነጋገሪያ ከሆኑ ዋል አደር ብለዋል።

የኢህአዴግ ውህደትን የሚደግፉት የግንባሩ አባሎችና አጋር ድርጅቶችም ሆኑ ህወሓት ኢህአዴግ እስከዛሬ በመጣበት መንገድ መቀጠል እንደማይችል ቢያምኑም ከዚህ ወዲህ ድርጅቱ እንዴት ይራመዳል? በሚለው ላይ መስማማት አልቻሉም።

ባለፈው ቅዳሜ የተደረገውን የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እሁድ ዕለት ከህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ያደረጉት ውይይት ፍሬ አልባ መሆን የዚህ ምስክር ነው።

ከዚህም በኋላ በነበሩት በቀጣዮቹ ቀናትም የሁለቱ ወገኖች ልዩነትና መካረር እንደቀጠለ ይመስላል።

ኢህአዴግና ህወሃት፡ 'አንድ ላይ ብንሆንም ተለያይተናል'

በተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ የቆዩት አቶ ሞሼ ሰሙ "ፖለቲካ እንደ ሒሳብ ይህ ከሆነ ያ ይሆናል የሚባል ስላይደለ ከዚህ ክስተት ውስጥ መጠቀም የሚቻልበት እድል እንዳለ ካመኑበት ሁለቱም ወገኖች ለንግግር ወደ ኋላ ሊመለሱ ይችላሉ" ብለው ያምናሉ።

በተቃራኒው በጠላትነት ስሜት ወደ መወነጃጀል የሚሄዱ ከሆነ ለመነጋገር የሚኖረውን እድል ያጠፋሉ ይላሉ።

"ከሁለቱም ወገን የሚጠበቀው ከስም መጠራራት፣ ከመወነጃጀልና አስቀያሚ መግለጫ ከማውጣት ሰከን ብለው ሁኔታዎችን መገምገም ነው። ያን ካደረጉ ሁል ጊዜ እድል አለ። እድሉን የሚወስኑት በተለይም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ከዚህ በኋላ በሚያራምዱት ፕሮፖጋንዳ ነው" ይላሉ አቶ ሞሼ።

ልዩነትና አለመግባባት ተፈጠረ ማለት አከተመለት፤ መነጋገር አይቻልም ማለት አይደለም። ልዩነቱ ደም ያፋሰሰ ሳይሆን የአሰራር፤ የርዕዮተ ዓለም ነው። ነገር ግን ይህንን ተቋቁመው በሰከነ መንገድ ነገሮችን መስመር አለማስያዝ የግንባሩ ፓርቲዎች መጥፊያም ሊሆን ይችላል የሚል ስጋታቸውንም ያስቀምጣሉ አቶ ሞሼ። ይህ ደግሞ ለአገሪቱም ለህዝቡም ከባድ ነው።

"ህወሓት ውስጥ ሆኖ እንጂ ወጥቶ አልነበርም መታገል የነበረበት" የሚል እምነት ላላቸው አቶ ሞሼ ህወሓት ቆርጦ ከኢህአዴግ የሚለይ ይመስልዎታል? የሚል ጥያቄ አቅርበን ነበር።

"ህወሃት ብቻውን ኖሯል ከዚህ ቀደም፣ ከብአዴን፣ ከኦህዴድና ከደኢህዴን ጋር አብሮ ሰርቷል። ሌሎቹ ባልነበሩበት ሁኔታ እነዚህ ፓርቲዎች የአገሪቱን ፖለቲካ ሲያንቀሳቅሱ ኖረዋል። ትልቁ ነገር ራስን ከተጨባጭ ሁኔታ ጋር ማዛመድ ነው። በሌላ በኩል ከህወሓት ውጪ ነገሮች ይሰራሉ ወይ? ብሎ መጠየቅም ያስፈልጋል።"

እሳቸው እንደሚሉት ራስን ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር የማዛመድ ነገር እንዳለ ሆኖ ህወሓት እንደሚለው የትግራይ ህዝብ መቶ በመቶ ከህወሓት ጋር ከሆነ ለኢህአዴግ የትግራይን ሕዝብ ሥነ ልቦና ማግኘት ቀላል አይሆንም።

ከህዝቡ ጋር ተነጋግሮና ተደማምጦ በኢትዮጵያ መፃኢ እድል ላይ ለመወሰን ያለው እድልም በጣም ጠባብ ይሆናል። ቁጥሩ ምንም ይሁን አንድም ክልል ከመንግሥት ጋር በሙሉ ልቡ አብሮ የማይሰራ ከሆነ ብዙ ጉዳቶች አሉት።

"ያልተግባቡት ፓርቲዎች ናቸው ስለዚህም የትግራይ ሕዝብ ልቡ መሸፈት የለበትም። የትግራይን ሕዝብ ማጣትም ቀላል ዋጋ አይደለም ብዬ አምናለሁ" ሲሉ አቶ ሙሼ ይጠቅሳሉ።

ለአቶ ሞሼ ልዩነቱ ዘላቂና ውስጣዊ አይደለም፤ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የኢህአዴግና የህወሓት ገመድ ተበጥሶ ይቀራል ብለውም አያምኑም። ይህ እምነታቸው የፓርቲ መሪዎቹ በረዥም የትግል ጉዞ ስላለፉ ለምክንያታዊነት ቦታ ይሰጣሉ በሚል እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው።

ህወሓትን እንደ ተቃዋሚ?

ህወሓት ከኢህአዴግ ከተለየ ቀጣይ እርምጃው ምን ይሆናል በሚለው ላይ የተለያዩ ሃሳቦች የተንፀባረቁ ሲሆን ተቃዋሚ ሆኖ ይቀጥላል የሚለው አንዱ ነው። አቶ ሞሼ ደግሞ "ከኢህአዴግ መውጣት ተቃዋሚ መሆን ነው ወይ?" ሲሉ ይጠይቃሉ።

"ያኛውም ወገን ተቃዋሚ ሊሆን ይችላል። ህወሓት ሌሎችን አስተባብሮ መንግሥት ሊሆን የሚችልበት እድል አብቅቷል ማለትም አይደለም" ሲሉ ነገሮች በሌላኛው አቅጣጫ ሊሄዱ የሚችሉበትም እድል እንዳለ ነው ይላሉ።

የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የህወሓት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ጌታቸው ረዳ ከቪኦኤ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የፓርቲው ቀጣይ እጣ ፋንታ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም በኢህአዴግ ሳይሆን በህወሓት፣ በደጋፊዎቹና በትግራይ ህዝብ የሚወሰን ነው ማለታቸው ይታወሳል።

ትግራይን 'አምሳለ አገር' ማድረግ

ባለፈው ሳምንት ትግራይን 'አምሳለ አገር' (Defacto State) የማድረግ ነገርን በተመለከት የህወሓት ልሳን በሆነው 'ወይን' መፅሔት ላይ የወጣው ጽሁፍ የኢህአዴግና የህወሓት ልዩነት መካረር ጥግን አመላክቷል ሊባል ይችላል።

ይህም 'የትግራይ መገንጠል' የሚለውን ሃሳብ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የብዙዎች መነጋገሪያ አጀንዳ አድርጎታል።

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆኑት አቶ መኮንን ፍስሃ ወይን ላይ የወጣው ጽሁፍ "ሙሉ በሙሉ የህወሃት አቋም ነው፤ አይደለምም ብሎ መደምደም ያስቸግረኛል፤ ነገር ግን የሚያሳየው አንድ ነገር ግን አለ" ይላሉ።

ይህ ሃሳብ ወይን ላይ ከመውጣቱ በፊት ጥቂት በማይባሉ የትግራይ አክቲቪስቶች፤ ምሁራንም ጭምር በግልፅ ሲንፀባረቅ ቆይቷል።

አቶ መኮንን እንደሚሉት ህወሃት ትግራይን የመገንጠል ሃሳብ ጨርሶ የለውም ብሎ ማለት አይቻልም። ለእሳቸው ይልቁንም 'ተገድጄ ወደዚህ አማራጭ ፊቴን ላዞር እችላለሁ' የሚል ነገር ይታያቸዋል። ይህም ቢሆን ግን ህወሓት ብቻውን የሚወስነው አይደለም።

እንደ አንድ ትግራዋይ በጉዳዩ ላይ የእሳቸው አቋም ምን እንደሆነ የጠየቅናቸው አቶ መኮንን "ታላቂቷን ትግራይ በታላቂቷ ኢትዮጵያ ነው የምፈልገው፤ ታላቅ ሲባል ሕዝብ ነው ታላቅ የሚሆነው" ነበር መልሳቸው።

ቢሆንም ግን 'ትግላችን እየተቀለበሰ ነው፤ እየተገፋን ነው' የሚል ስሜት በትግራይ ሕዝብ ዘንድ በስፋት እንዳለ ያስረግጣሉ አቶ መኮንን።

በትክክል ምን ያህሉ የትግራይ ሕዝብ መገንጠልን ይደግፋል? የሚለው ጥልቅ ጥናት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው።

ኢህአዴግ ካልተስማማ ይፈርሳል፤ መፍረስም አለበት ይህ ግን የኢትዮጵያን እጣ መወሰን የለበትም የሚል አቋም ያላቸው አቶ መኮንን "ሞቱ አልታወጀም እንጂ ኢህአዴግ ከሞተ ቆየ እኮ" ይላሉ።

አባልም አጋርም ድርጅቶች በውህደቱ እኩል ይወስናሉ

በኢህአዴግ ጽህፈት ቤት የግንባሩን ውህደት ያጠናው ቡድን መሪ የሆኑት ዶ/ር ተመስገን ቡርቃ ከዚህ በፊትም ሲያራምዱ የነበረው የኢህአዴግን ፖሊሲና ስትራቴጂ ስለሆነ አባል ድርጅቶች ብቻ ሳይሆኑ አጋር ድርጅቶችም እራሳቸውን አፍርሰው በእኩል ደረጃ መጥተው ብልፅግና ፓርቲን እንደሚመሰርቱ ለቢቢሲ አብራርተዋል።

"ኢህአዴግ ፓርቲውን መስርቶ የሚያመጣቸው ሳይሆን እኩል ተደራድረው የሚመሰርቱት ነው የሚሆነው። የእኛ ጥናት ይሄን ነው የሚያመለክተው እነሱ የሚወስኑትን እናያለን" ይላሉ ዶ/ር ተመስገን።

ውህደቱ በይፋ ሊታወጅ ስለሚችልበት ጊዜ በተደረገው ጥናት ላይ የተቀመጠ ነገር መኖሩን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር ተመስገን "ችግሮችን ለመፍታት እኛ አሁኑኑ ተዋሃዱ ነበር ያልነው፤ ግን ያው ውሳኔው የፖለቲካ ነው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ውህደትና የህወሓት ቀጣይ ዕጣ

አገሪቱን ለሦስት አስርት ዓመታት ያስተዳደረውን ግንባር ጸንሶ በመውለድ ዋኛውን ድርሻ የሚወስደው ህወሓት በፈጠረው ድርጅት ቀጣይ ውህድ ህላዌ ላይ አብሮ እንደማይሳተፍ አሳውቋል።

ቀሪዎቹ የግንባሩ አባላትና አጋር ድርጅቶችም ውህደቱን እውን ለማድረግ አስፈላጊ የሆኑ ሂደቶችን በፍጥነት እያከናወኑ ነው። በግንባሩ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ የጀመረው የውሳኔው ሂደት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በምክር ቤቱ ውሳኔ ወደ ቀጣዩ ደረጃ ተሸጋግሯል።

ከዚህ በኋላም ድርጅቶቹ ከአባሎቻቸው ጋር ወስነው የውህደቱን ጥያቄ ወደ ጠቅላላ ጉባኤው በመውሰድ የመጨረሻውን እልባት ይሸጡታል። ይህም እስካሁን በነበረው ሂደት እምብዛም እንቅፋት የሚገጥመው አይመስልም።

ህወሓትም እስካሁን ባለው አቋም ከቀጠለ በውህደቱ ላይ አሉኝ የሚላቸውን የሕግ ጥያቄዎች በማንሳት ሊሞግት ይችላል። ከዚህ ባሻገርም ከዚህ በፊት አንዳንድ አባላቱ እንደጠቆሙት ከሌሎች የፖለቲካ ቡድኖች ጋር በመቀናጀት አዲሱን ውህድ ፓርቲ የሚገዳደር አገራዊ ግንባር አሊያም ጥምረት በመመስረት በቀጣይ ምርጫ ላይ ሊቀርብ እንደሚችል ይጠበቃል።

እስካሁን በወሰዳቸው አቋሞች ግን ህወሓት እራሱን አክስሞ ከቀድሞ የወታደራዊና የፖለቲካ ትግል አጋሮቹ ጋር የብልጽግና ፓርቲ አባል የመሆን እድሉ በጣም የጠበበ ነው።

ከዚህ አንጻር ኢህአዴግ በውህደት እርምጃው የሚቀጥል ከሆነ ህወሓት በውህድ ፓርቲው ውስጥ የመኖሩ ነገር እምብዛም የሚታሰብ አይሆንም። ለሁሉም ግን በቀጣይ ቀናት የፖለቲካ ቡድኖቹ የሚደርሱበት ውሳኔ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ወሳኝ መስመሮችን የሚያሰምር ይሆናል።