የእንግሊዝ ልዩ ሃይሎች የአፍጋን ህፃናትን ገድለዋል?

እንደ አውሮፓውያኑ በ2012 የእንግሊዝ ልዩ ሃይል በአንድ የአፍጋኒስታን መንደር አራት ልጆችን መግደሉን እና ለዚህ የጦር ወንጀል ማንም ተጠያቂ ሳይሆን መቅረቱን የህፃናቱ ቤተሰቦች ይናገራሉ። እነዚህ ቤተሰቦች እንዳሉት ከአራቱ ልጆች ሶስቱ ህፃናት ናቸው።

የአይን እማኞች እንደገለፁት የ12 ዓመቱ አህመድ ሻህ፣ የ14 ዓመቱ ሞሃመድ ታይብ ከ17 ዓመቱ ኔክ ሞሃመድና ወንድሙ ፋዘል ጋር ለማምሸት ወደ ወንድማማቾቹ ቤት አምርተው ነበር። ምሽት ሁለት ሰዓት ገደማ የአፍጋን እና የእንግሊዝ ወታደሮች ወደ ሎይ ባህ ወደ ተሰኘው መንደር ተገኝተው ነበር። የእንግሊዝ ልዩ ሃይሎች ባለ አንድ መኝታ ክፍል ወደ ሆነው የእነዚህ ቤተሰቦች እንግዳ ቤት በመግባት ተኩስ ከፈቱ።

የሁለቱ ልጆች እናት ሳባህ ወደ እንግዳ ቤቱ ስትገባ የህፃናቱ አጥንትና ጥርስ ተበታትኖ ፣ሊጠጡ የቀዱት ሻይ ደም ተሞልቶ ባለበት እንደነበር ትናገራለች።

ልጆቹ ጭንቅላታቸው ላይ መመታታቸውን እና ሌሉቱን ሙሉ ከአራቱ አስከሬን ጋር በዚያ የእንግዳ ማረፊያ ማደሯን ታስታውሳለች።

ጥቃቱ ኢላማ የነበረው ከተገደሉት አራት ልጆች አንዱ ፋዘል ሞሃመድ እንደነበር የአፍጋን ደህንነት ኤጀንሲ ቢያስታውቅም የአካባቢው አስተዳዳሪ ፋዘል የታሊባን ኮማንደር ነው የሚለው ነገር ፈፅሞ ሊሆን የማይችል ነገር እንደሆነ ተናግረዋል።

በሰንደይ ታይምስና በቢቢሲ ፓኖራማ ጥምረት የተሰራ የምርመራ ዘገባ በዚህ ጉዳይ የጦር ወንጀል መፈፀሙን የሚያመለክቱ መረጃዎችን አውጥቷል።

እነዚህን አራት ልጆች የቀጠፈ አይነት ጥቃት ታሊባን ላይ ያነጣጠረ ሲሆን በአፍጋኒስታን ጦርነት ወቅት በስፋት ተግባራዊ ሆኗል።

እንዲህ ያለው የምሽት ጥቃት ኢላማ ቢኖርም ባይኖርም የሚፈፀም መግደል ወይም መያዝን ያለመ እንደሆነ ፍራንክ ሊድ ሊድዊጅ የተባሉ የጦርነት ኤክስፐረት ይገልፃሉ።

በዚህ ዓይነቱ የምሽት ጥቃት አብዛኛውን ጊዜ ኢላማ የሚሆኑት የታሊባን አባላት ቢሆኑም ኢላማዎች ሁሌም ትክክል አለመሆናቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ። በዚህ ምክንያት በርካታ ሰላማዊ ሰዎች ስለመገደላቸው ለተባበሩት መንግሥታት የቀረቡ ማስረጃዎች አሉ።

በመጨረሻም ተመድ የእንግሊዝ ልዩ ሃይል እና የአፍጋኒስታን ጦር አንድ ላይ ሆነው በዚህ ዓይነቱ ጥቃት 300 ንፁሃን ዜጎችን እንደገደሉ ይፋ አድርጓል።