ለመኖሪያ ቤት ኪራይ ቀብድ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚጠየቅባት ከተማ

የፎቶው ባለመብት, GLORIA YUSUFF
አቅምን ያገናዘበ አነስ ያለ ጎጆ ፈልጎ እንደው የራስ ንብረት ማድረግ ባይቻል እንኳ መከራየት የወጣቶች ራስ ምታት ከሆነ ሰንበትበት አለ።
በናይጄሪያዋ የንግድ ከተማ ሌጎስ ውስጥ አነስ ያለች ክፍል ለመከራየት ግማሽ ሚሊዮን ብር ያስፈልግዎታል።
ቪክቶሪያ አይላንድ በተሰኘችው የሌጎስ ቅልጥ ያለች ክፍል ባለሁለት መኝታ ቤተ መከራየት ፈለጉ እንበል። በትንሹ እስከ 22 ሺህ ዶላር [ግማሽ ሚሊዮን ብር ገደማ] ቅድሚያ ክፍያ መጠየቅዎ ሳይታለም የተፈታ ነው።
ታድያ ይህ የሚጠየቀው ቅድሚያ ክፍያ ዓመታዊ ነው። ከ5 ሺህ ዶላር ጀምሮ እስከ 40 ሺህ ዶላር ድረስ ሊጠየቁ ይችላሉ። ታድያ ኑሮ እንደ ቀትር ፀሐይ በሚፋጅባት ሌጎስ አከራዮች የሚጠይቁትን ዶላር ይዞ መገኘት ለወጣቶች እጅግ ከባድ ነው።
አከራዮች ይህን ያህል ገንዘብ የሚጠይቁበት ምክንያት ሌጎስ ውስጥ የመሬት እና የግንባታ ዋጋ እጅግ ከበድ ያለ በመሆኑ ነው።
ቤት መከራየት ለሚሹ ወጣቶች የሚሆን አነስ ያለ ባለአንድ ክፍል ወይም ባለአንድ መኝታ ቤት ማግኘትም የማይታሰብባት ከተማ ናት፤ ሌጎስ።
ዓመታዊ ቅድመ ክፍያ
አከራዮች ቀድመው ማስከፈልን ይመርጣሉ፤ ለዚያውም ዓመታዊ። የኪራይ ዋጋ 5 ሺህ ብር ከሆነ ዓመታዊ ሂሳብ 60 ሺህ ይሆናል። ይህንን ግንዘብ 'ሆጭ' ማድረግ የማይችል ተከራይ ውሃ በላው ማለት ነው።
እንደውም አሁን ሕጉ ተሻሽሎ እንጂ አከራዮች የሁለት ዓመት ቅድመ ክፍያ መጠየቅ ይችሉ ነበር። ይህንን የቤት ኪራይ ራስ ምታት መቋቋም ያቃታቸው የሌጎስ ወጣቶች ታድያ ያላቸው አማራጭ ሰብሰብ ብለው በጋራ መኖር ነው።
ከተመረቀ በኋላ መኖሪያ ቤት ማግኘት ሥራ ከማግኘት እኩል የከበደው ኦሉዋፌሚ ከሌሎች 10 አጋሮቹ ጋር በመሆን ምንጣፍ ዘርግቶ ይተኛ ነበር።
ከቤት ኪራይ እኩል ሌላኛው የሌጎስ ቤት ፍለጋ መከራ ለኮረንቲ እና ውሃ የሚጠየቀው ዋጋ ነው። አከራይ ከፈቀደ ለውሃ እና ለመብራት ከቤት ኪራይ ሂሳብ ላይ ቀነሶ ይከፍላል። አይሆንም ካለ ግን ተከራይ የውሃ እና መብራት ወጪን መሸፈን ግዴታው ነው።
ይህንን ችግር ያስተዋሉ ወጣቶች ተሰባስበው አንድ ድርጅት አቋቋሙ፤ ፋይበር የሚባል። ይህ አከራይ እና ተከራይን በበይነ-መረብ የሚያጣምር ድርጅት የቅድሚያ ክፍያን ለማስቀረትና ወጣቶች የሚሿቸውን ብዙም ያልተቀናጡ መኖሪያ ቤቶችን ለማቅረብ ቆርጦ ተነስቷል።
ድርጅቱ 200 አከራዮች አሉት። ቤት ለመከራየት ተመዝግበው የሚጠብቁ 2000 ደንበኞችን ይዟል። እርግጥ ነው ሚሊዮኖች ለሚኖሩባት ሌጎስ ይህ ውቅያኖስን በማንኪያ እንደ መጭለፍ ቢሆንም ወጣቶቹ ያ'ቅማቸውን እያደረጉ እንዳሉ ብዙዎች ይከራከራሉ።
'የኮራ የደራ ሥራ ያለኝ ነኝ፤ ደሞዜም ወፍራም ነው' ብሎ ኪራይን በወር ለመክፈል ማሳመን የማይታሰብ ነው።
ቢሆንም ሌጎስ ቀንም ማታም ሚስማር ስትመታ፤ ሲሚንቶ ስታቦካ ነው ውላ የምታድረው። የሪል ስቴት ባለቤቶች ለወጣቶች የሚሆን አነስተኛ ክፍል ወይም ባለአንድ መኝታ ክፍል ቤቶች እየሠሩ ነው። ምናልባት እኒህ ግንባታዎች ሲጠናቀቁ የሌጎስ ወጣቶች ችግር ይቀረፍ ይሆናል።














