ከ10 ዓመት በፊት ጠ/ሚ ዐብይ መረጃ አቀብለውት እንደነበር ኦነግ ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Social media
ጠቅላይ ሚንስር ዐብይ አህመድ ከ11 ዓመት በፊት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የምዕራብ ዕዝ መሪ በነበረው ለገሰ ወጊ ላይ መንግሥት ሊፈጽም አቅዶት የነበረውን ጥቃት በተመለከተ ለግንባሩ አመራር መረጃ አቀብለው እንደነበረ ግንባሩ ገለጸ።
ኦነግ አርብ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስት ከጥቃቱ ቀደም ብለው በግንባሩ የጦር መሪ ላይ ሊፈጸም ስለታቀደው ጥቃት መረጃ በውጪ ለሚገኙት አመራሮች መስጠታቸውን አረጋግጧል።
ለገሰ ወጊ የተገደለው ከ10 ዓመት በፊት የነበረ ሲሆን ግድያው እንዴት እንደተፈጸመ በጊዜው ዘጋቢ ፊልም ተዘጋጅቶ በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ተላልፎ እንደነበር ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰሞኑን ከከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተከስቶ የ78 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈውን ጥቃትና ግጭት ለማረጋጋት ከህዝብ ጋር ውይይት ባካሄዱበት ወቅት መቀመጫውን ኤርትራ አድርጎ ከነበረው ኦነግ ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት ጠቅሰው እንደነበር ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
ረቡዕ ዕለት በሐረር ከተማ በተካሄደው የውይይት መድርክ ላይ ይህንን ጉዳይ የሚያመላክት ነገር አንስተው የነበረ ሲሆን ሐሙስ አምቦ ከተማ ውስጥ በተደረገው ተመሳሳይ ውይይት ላይ ደግሞ ስለ ለገሰ ወጊ ማንሳታቸውን ተጠቅሷል።
የግንባሩ መግለጫ ከዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ውስጥ ሲሰሩ በነበሩበት ወቅት መንግሥት በምዕራብ የአገሪቱ ክፍል ሲንቀሳቀስ በነበረው የኦነግ ቡድን ላይ ዘመቻ ሊያካሂድ እንደነበረ መናገራቸውን ይገልጻል።
ኦነግ አሁን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ዐብይ አህመድ በወቅቱ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ለገሰ ወጊ የተባለውን የግንባሩ ጦር መሪን ለመግደል ክትትል እየተደረገ መሆኑን መረጃ እንደሰጡት አምኖ፤ ነገር ግን በወቅቱ በመረጃው መሰረት ለገሰ ወጊ ከጥቃቱ እራሱን እንዲያድን በአመራሩ ቢነገረውም እሱ ግን የእራሱን ውሳኔ መውሰዱን መግለጫው ያመለክታል።
ነገር ግን የኦሮሞ ነጸነት ግንባር በመግለጫው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚያ ወቅት እንዳደረጉት ዛሬ መንግሥታቸው ከግንባሩ ጋር ተቀራርቦ ከመስራት አንጻር ጉድለቶች እንዳሉ ገልጿል።
ኦነግ በመግለጫው "ህዝቡ አሁን ያለውን መንግሥት ለኦሮሞ ፖለቲካ አዲስ ነው በሚል የሚያቀርበውን ትችት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ሲል ለኦነግ የሰጡትን መረጃ ለዚህ እንደምላሽ እየተጠቀሙበት ሊሆን ይችላል" ብሎ እንደሚያምን ጠቅሷል።
የኦነግ ከፍተኛ አመራር ከሆኑት መካከል አንዱ አቶ ሚካኤል ቦረን ለዚህ መግለጫ መውጣት ሦስት ምክንያቶች እንዳሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በተደጋጋሚ የለገሰን ግድያና ከኦነግ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ማንሳታቸው ለትግሉ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው የሚያሳይ ቢሆንም ሌላ የሚያመለክተው ነገር አለ ብለው አቶ ሚካኤል ያምናሉ "ለለገሰ መገደል በእኛ በኩል ጉድለት እንዳለ ለማስመሰልና አላስፈላጊ ጥርጣሬ ህብረተሰቡ ውስጥ ሊፈጥር ይችላል" ይላሉ።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስላበረከቱት አስተዋጽኦ በማንሳታቸው ደስተኛ የሆነ እንደማይመስል የአቶ ሚካኤል ቦረን ንግግር ያመለክታል።
"ይህን ጉዳይ በተደጋጋሚ ማንሳታቸው ለምን አስፈለገ? ህዝቡ እንዳይሳሳትም የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል እንደነበር ለማስቀመጥ ነው አሁን መግለጫውን ያወጣነው" ይላሉ።
አቶ ሚካኤል አክለውም "ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምን ስለለገሰ ብቻ ያነሳሉ?" በማለት ጠይቀው "አገር የሚያስተዳድር መንግሥት ለረጅም ዓመታት በግንባሩ አባላት ላይ ጥቃት ሲያካሂድ እንደቆየና አሁንም በዚህ ወቅት ጥቃቱ እንዳልቆመ" ይናገራሉ።
ሲያጠቃልሉም "ከዚህ በፊት ለገሰን በተመለከተ ስላደረጉት ነገር ከሚናገሩ ይልቅ ዛሬ ስልጣን በእጃቸው እያለና የኦነግ አመራር አዲስ አበባ ውስጥ ባለበት ጊዜ፤ ዛሬ ከዚያ የበለጠ መስራት ይቻላል" ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት በኦሮሞ ነጻነት ግንባር መግለጫ ላይ ስለተጠቀሰው ጉዳይ እስካሁን ያለው ነገር የለም።

















