በፍትሕ ሥርዓቱ የተማረሩት ታይላንዳዊ ዳኛ ራሳቸው ላይ ተኮሱ

ታይላንዳዊው ዳኛ በአገሪቷ ውስጥ ያለውን የፍትሕ ሥርዓት አስመልክቶ ትችት አዘል ያልተለመደ ንግግር ካደረጉ በኋላ በፍርድ ቤቱ ውስጥ ራሳቸው ላይ ተኩሰዋል።

ካናኮርን ፒያንቻናው በታይላንድ ደቡባዊ ግዛት ያላ በተባለ ፍርድ ቤት በዳኝነት ይሠሩ ነበር።

ባሳለፍነው አርብ በመግደል ወንጀል የተጠረጠሩ አምስት ሙስሊም ወንዶችን ነፃ እንዲወጡ ውሳኔ ያስተላለፉት ዳኛው ለገለልተኛ የፍትሕ ሥርዓት ለዳኞች ጥሪ አድርገው ነበር።

ታዲያ በዚህ ወቅት ነበር የገቡትን ቃለ መሃላ አውጥተው ካነበቡ በኋላ ሽጉጣቸውን መዘዝ አድርገው ደረታቸው ላይ የተኮሱት።

ዳኛው በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ከማድረጋቸው አስቀድሞ፤ በእርሳቸው እንደተፃፈ በተነገረው ማስታወሻቸው ላይ ራሳቸውን ለማጥፋት መወሰናቸው በያዙት የክስ መዝገብ ላይ ጣልቃ ለመግባት ከሚደረጉ ሙከራዎች ጋር የተገናኘ እንደሆነ ያስረዳል።

ከሞት በተዓምር የተረፉት እኝህ ዳኛ ወደ ሆስፒታል ተወስደው ከጉዳታቸውም እያገገሙ እንደሆነ ተነግሯል።

"አንድን ግለሰብ ለመቅጣት ግልፅ እና ተጨባጭ ማስረጃ እንፈልጋለን፤ ለዚህ እርግጠኛ ካልሆናችሁ ቅጣት እንዳትጥሉባቸው" ሲሉ አስገንዝበዋል።

ዳኛው አክለውም "ይህን ስል አምስቱ ተከሳሾች ወንጀሉን አልፈፀሙትም እያልኩ አይደለም፤ ድርጊቱን ፈፅመውትም ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን የፍርድ ሂደቱ ግልፅና ተጨባች መሆን አለበት፤ ያላጠፉ ሰዎችን መቅጣት 'አይጥ በበላ ዳዋ ተመታ' ነው የሚሆነው" ብለዋል።

በፌስቡክ በቀጥታ ሲተላለፍ የነበረው የዳኛው ንግግር ድንገት የተቋረጠ ሲሆን በፍርድ ቤቱ የነበሩ ሰዎች እንዳሉት ግን ዳኛው ራሳቸው ላይ ከመተኮሳቸው በፊት በታይላንዱ ንጉስ ፎቶግራፍ ፊትለፊት በመቆም የገቡትን ቃለ መሃላ ሲያነቡ ነበር።

ዳኛ ካናኮርን በራሳቸው ሕይወት ላይ ለምን እንደፈረዱ በግልፅ የታወቀ ነገር የለም።

የፍርድ ቤቱ ቃል አቀባይ ሱሪያን ሆንግቪላይ፤ ዳኛው ራሳቸው ላይ የተኮሱት በግል ባለባቸው "ጭንቀት" ምክንያት እንደሆነ ለኤ ኤፍ ፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ዳኛው ከያዙት የክስ መዝገብ ጋር በተገናኘ በደረሰባቸው ጫና ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

እርሳቸው እንደፃፉት በተነገረው እና በፌስቡክ ላይ በተሠራጨው ማስታወሻቸው ላይ የአምስቱ ሙስሊሞች የክስ መዝገብ ላይ ለመወሰን በቂ ማስረጃ ባያገኙም ፍርድ እንዲያስተላልፉባቸው ግፊት ይደረግባቸው እንደነበር ያመላክታል።

"በዚህ ወቅት ሌሎች በአገሪቷ የሚገኙ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ዳኞችም እንደ እኔ ተመሳሳይ ድርጊት ይፈፀምባቸው ይሆናል" ሲሉ ስጋታቸውን በፃፉት ማስታወሻቸው ላይ አስፍረዋል።

"የገባሁትን ቃለ መሃላ ካልጠበቅኩ፤ ያለ ክብር ከምኖር፤ ሞቴን እመርጣለሁ" ብለዋል ዳኛው።

በታይላንድ የፍትሕ ሥርዓት ላይ ዳኞች ትችት መሰንዘራቸው የተለመደ አይደለም።

የመብት ተሟጋች ቡድኖች በአብዛኛው ሙስሊም በሚኖሩበት ማላይ ግዛት በሙስሊም ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ የመሠረቱት የፀጥታ ኃይሎች ናቸው ሲሉ ይከሳሉ።